የኢህአዴግ ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር ምርጫ ባለፉት ስድስት ወራት መልካም ሥራዎች መሰራታቸውን ያሳያል- አስተያየት ሰጪዎች

78
አዲስ አበባ መስከረም 26/2011 በ11ኛው የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባኤ የዶክተር አቢይ አህመድና አቶ ደመቀ መኮንን መመረጥ  ብሔራዊ ድርጅቶቹ በአገሪቱ የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል ቁርጠኝነታቸውን  ያሳዩበት መሆኑን  የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡ ኢዜአ ያነጋገራቸው የከተማው ነዋሪ አቶ ብርሃኑ ወዳጆ እንደተናገሩት በጉባኤው ሁለቱ መሪዎች ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር ሆነው መመረጣቸው ባለፉት ስድስት ወራት በአገሪቱ መልካም ስራዎች መሰራታቸውን ያሳያል፡፡ ከቤተሰቦቻቸው ጋር  ውጤቱን በጉጉት ሲጠባበቁ  እንደነበረ የተናገሩት አቶ ብርሀኑ ውጤቱ እንዳስደሰታቸውና የሁለቱ መሪዎች መመረጥ ለነገ የአገሪቱ ሰላምና ሁለንተናዊ እድገት ከፍተኛ ጠቀሜታ አለውም ብለዋል፡፡ ሁለቱም መሪዎች ያገኙት ድምጽ ሁሉም የኢህአዴግ እህት ድርጅቶች የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል ያላቸው ፍላጎትና አንድነት የተስተዋለበት እንደሆነም ጨምረው ገልፀዋል ፡፡ ሌላዋ አስተያየት ሰጪ ወጣት ለን አዝማ  በምርጫው እንደተደሰተች ገልፃ  ዘረኝነትን በማስወገድ  ለአገራችን እድገት ብልጽግናና ሰላም ተረባርበን በመስራት የተጀመረውን ለውጥ  ማገዝ ይገባናል ብላለች፡፡ መንግስት ለወጣቶች  እና ሴቶች የሰጠውን ትኩረት በማጠናከር በቀጣይም በስራ እድል ፈጠራና በሌሎች  የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን  በሚያጎለብቱ ጉዳዮች ላይ መስራት እንደሚገባም ጠቁማለች። በአገሪቱ ለውጦች ቢኖሩም አሁንም በተለይ በአንዳንድ አካባቢዎች  የሚታዩ ግጭቶችና መፈናቀሎች አሳሳቢ መሆናቸውን  የጠቀሰው ወጣት አሸናፊ ሀይለእየሱስ በበኩሉ  እነዚህንና ሌሎች ችግሮችን ለመፍታት  በጉባኤው የተወሰደው አቋም መፍትሔ  ሊሆን ይችላል የሚል እምነት እንዳለው ተናግሯል። “ወጣቱ የተጀመረውን ለውጥ  ለማስቀጠልና የአገሪቱን ሰላም ለማይፈልጉና ለውጡ ለማይመቻቸው አካላትመታለል መጠቀሚያ  መሆን የለበትም” ያሉው ወጣት አሸናፊ  ህብረተሰቡ  በተለይ በማህበራዊ ሚዲያ የሚወጡ መረጃዎችን አጣርቶ በመጠቀም ለሰላሙ ዘብ መቆም አለበት ብሏል፡፡ የሃይማኖት አባት አባ ዮሐንስ ገብረህይወት በበኩላቸው መንግስትና ሃይማኖትን ሰላምና ልማት እንደሚያገናኛቸው ጠቅሰው  ሁለቱም በጋራ መሥራት እንደሚገባቸው ተናግረዋል። በአገሪቱ ሰላም እንዲሰፍንና ፍቅር እንዲሰፋ የሃይማኖት ተቋማት ሃላፊነታቸውን  ሊወጡ ይገባልም ብለዋል። በሀዋሳ ለሶስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የኢህአዴግ 11 ጉባኤ ትላንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድን የድርጅቱ ሊቀመንበር እና አቶ ደመቀ መኮንን ምክትል ሊቀመንበር አድርጎ መምረጡ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም