ክለቦች የሜዳ ላይ ረብሻን በመከላከል ኃላፊነታቸውን ካልተወጡ እርምጃ ይወሰድባቸዋል-የኢትዮጵያ  እግር ኳስ ፌዴሬሽን

631

አዲስ አበባ መስከረም 26/2011 ክለቦች የሜዳ ላይ ረብሻና ሁከትን በመከላከሉ በኩል ኃላፊነታቸው ካልተወጡ እስከ ነጥብ ቅነሳ የሚደርስ እርምጃ እንደሚወስድ የኢትዮጵያ  እግር ኳስ ፌዴሬሽን ገለጸ።

ፌዴሬሽኑ የ2010 ዓ.ም የፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ ክለቦች ግምገማና የ2011 ዓ.ም የፕሪሚየር ሊግ የእግር ኳስ ክለቦች የዕጣ ማውጣት ስነ-ስርዓት አካሂዷል።

የፌዴሬሽኑ የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰለሞን ገብረስላሴ የ2010 ዓመት ፈታኝ ጊዜ እንደነበር ጠቅሰው፤ እንደማሳያም የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል ችግሮችና የውድድሮች መቆራረጥን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ኮሎኔል አወል አብዱራሂም ከዚህ በኋላ ፌዴሬሽኑ ሁከት ፈጣሪዎችን እንደማይታገስ አስታውቀዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የእግር ኳስ ሜዳዎች ላይ ህገወጥ ተግባር እየተለመደ መምጣቱንና ድርጊቱ ለስፖርቱ ፀር የሆነ አፍራሽ ድርጊት ነው ብለዋል።

በመሆኑም ከዚህ በኋላ ስፖርትን ተገን በማድረግ ሁከት የሚፈጠር ማንኛውንም አካል ከባድ ቅጣት እንደሚተላለፍበትና በጨዋነት ለሚያጠናቅቁም እውቅናና ሽልማት እንደሚሰጥ አስታውቀዋል።

ክለቦች በሜዳቸው የሚደረግ ጨዋታ በሰላም እንዲጠናቀቅ የማያደርጉ ከሆነ እስከ ነጥብ ቅንሳ የሚደርስ ቅጣት ይጣልባቸዋል፤ በስፖርታዊ ጨዋነት ለሚያጠናቅቁት ደግሞ ሽልማት ይበርከትላቸዋል ተብሏል።

ከዚህ በተጨማሪ ክለቦች ለስፖርታዊ ጨዋነት የሚሰጣቸው ነጥብ ለሻምፒዮንነት እንደ አንድ መስፈርት የሚያገለግል መሆኑን በመገንዘብ ጨዋታዎች በሰላም እንዲጠናቀቁ የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው ብለዋል።