የኦሮሚያ ክልል መንግስት በድርቅ የተጎዱ ወገኖችን በመደገፍ ረገድ እያከናወነ ባለው ስራ ላይ የኀብረተሰቡ ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቀረበ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 19/2015 የኦሮሚያ ክልል መንግስት በድርቅ የተጎዱ ወገኖችን በመደገፍ ረገድ እያከናወነ ባለው ስራ ላይ የኀብረተሰቡ ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቀረበ፡፡

የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አወሉ አብዲ በክልሉ በድርቅ አደጋ ለተጎዱ ዜጎች እየተደረገ ያለውን ድጋፍ አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ 

በመግለጫቸውም በክልሉ አስር ዞኖች ለሶስት ዓመታት ዝናብ ባለመጣሉ የድርቅ አደጋ መከሰቱን ገልጸዋል። 

በዚህም በክልሉ በድርቅ ለተጎዱ ከ4 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ገልፀው፤ የተረጂዎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ የተጠናከረ ድጋፍ ያስፈልጋል ብለዋል። 

እስካሁን ከ2 ሚሊዮን በላይ ኩንታል የተለያዩ የእህል አይነቶች ድጋፍ ተደርጓል ነው ያሉት፡፡

መንግስት እና ህብረተሰቡ እያደረጉት ባለው ድጋፍ በድርቁ ምክንያት የአንድም ሰው ህይወት አለማለፉን ገልጸዋል፡፡ 

በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች በድርቁ ሰው እንደሞተ በማስመሰል ሀሰተኛ መረጃዎች እየተናፈሱ መሆኑን ጠቅሰው፤ ድርቁን ምክንያት በማድረግ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ አስጠንቅቀዋል፡፡ 

በተለይ በቦረና ዞን የድርቁ ሁኔታ አሳሳቢ በመሆኑ ህዝቡ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል። 

እስከአሁን ለተደረገው ድጋፍ አመስግነው በአገር ውስጥ እና በውጪ የሚኖሩ ዜጎች ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ምክትል ርዕሰ-መስተዳድሩ ጥሪ አቅርበዋል። 

በድርቅ አደጋ ምክንያት የሚደርሰውን ጉዳት በዘላቂነት ለመከላከል በውሃ ልማት፣ በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራዎች ላይ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል። 

የኦሮሚያ ቡሳ ጎኖፋ በድርቅ ለተጎዱ ዜጎች ድጋፍ የሚሰባሰብበትን የባንክ ሂሳብ ቁጥር የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1000007343756፣ ሲንቄ ባንክ 1029565101201 ሲሆን በቀጣይ በሌሎች ባንኮች የሂሳብ ቁጥር ይከፈታል ሲሉም ጠቁመዋል። 

ባለፈው ዓመት ብቻ በድርቅና በሰው ሰራሽ አደጋዎች ለተጎዱት 7 ነጥብ 3 ሚሊዮን ህዝብ ድጋፍ መደረጉን አስታውሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም