የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ ከቻይና የገንዘብ ሚኒስትር ሊዩ ኩን ጋር ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ ከቻይና የገንዘብ ሚኒስትር ሊዩ ኩን ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 19/2015 የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ ከቻይና የገንዘብ ሚኒስትር ሊዩ ኩን ጋር በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የኢኮኖሚ አጋርነት በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ድህነትን ለማሸነፍ ለምታደርገው ትግል እና ለአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ቻይና የምታደርገው የማያቋርጥ ድጋፍ የሚደነቅ መሆኑን አቶ አህመድ ገልፀዋል፡፡

የቻይና - አፍሪካ የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን የገለፁት ሚኒስትሩ፤ ግንኙነቱ በመከባበር፣ በጋራ ጥቅምና በፖሊሲ ነፃነት ላይ የተመሰረተ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
የቻይና የገንዘብ ሚኒስትር ሊዩ ኩን በበኩላቸው የቻይናን የኢኮኖሚ እድገት እና የልማት ተሞክሮዎቿን አንስተው፤ ሀገሪቱ በአጭር ጊዜ ከ800 ሚሊዮን በላይ ዜጎቿን ከድህነት ማውጣት የቻለችበትን የልማት ስኬት ማብራራታቸውን በቻይና የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስታውቋል።
የሁለቱን ሀገራት ኢኮኖሚያዊ ትስስር የበለጠ ለማሳደግ ከኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በቅርበት እንደሚሰሩም ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።