የኢትዮጵያንና ሞሮኮን ሁለትዮሸ ግንኙነት ይበልጥ በፋይናንስ ዘርፍ ለማስተሳሰር እየተሰራ ነው - አምባሳደር ኢሳያስ ጎታ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያንና ሞሮኮን ሁለትዮሸ ግንኙነት ይበልጥ በፋይናንስ ዘርፍ ለማስተሳሰር እየተሰራ ነው - አምባሳደር ኢሳያስ ጎታ

የካቲት 17/ 2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያንና ሞሮኮን ሁለትዮሸ ግንኙነት ይበልጥ በፋይናንስ ለማስተሳሰር እየተሰራ መሆኑን በሞሮኮ የኢትዮጵያ አምባሳደር ኢሳያስ ጎታ ገለጹ፡፡
ኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፏን ለውጭ ኢንቨስትመንት ክፍት ለማድረግ እያከናወነችው ያለው ስራም የአገራቱን ግንኙነቱ ለማጠናከር ትልቅ እድል እንደሚከፍት ጠቁመዋል፡፡
በሞሮኮ የኢትዮጵያ አምባሳደር ኢሳያስ ጎታ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያና ሞሮኮ ረዥም ዓመታትን ያስቆጠረ የዲፕሎማሲ ግንኙነት አላቸው፡፡
የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ለመመስረት ሲደረግ በነበረው ተጋድሎም የአህጉሪቷ መሪዎች በካዛብላንካና ሞኖሮቪያ ቡድኖች የነበረውን መከፋፈል በማቀራረብ ከፍተኛ ሚና እንደነበራቸው አስታውሰዋል።
በወቅቱም ቀዳማዊ ግርማዊ ኃይለስላሴ እና ከሞሮኮው ንጉስ ግርማዊ ሀሰን 2ኛ ጋር በመሆን ሁለቱ ቡድኖች ልዩነታችውን በመፍታት የአፍሪካ አንድነት ምስረታ እውን እንዲሆን የአንበሳውን ድርሻ እንደተወጡም ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድም ለግርማዊ ሀሰን 2ኛ ቤተሰቦች ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ለነበራቸው ሚና የሰጡትን ዕውቅና በሞሮኳዊያን ዘንድ ከፍተኛ ቦታ እንደተሰጠው አንስተዋል።
እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ2016 በአሁኑ የሞሮኮ ንጉስ ግርማዊ ሙሀመድ 6ኛ የተመራ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በኢትዮጵያ ያደረገው የስራ ጉብኝትም የአገራቱን ጥብቅ ወዳጅነት የሚያሳይ እንደሆነ ገልጸዋል።
ሞሮኮ ከደቡብ አፍሪካ በመቀጠል የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በመሳብና በማመንጨት ሁለተኛ አፍሪካዊት አገር መሆኗን ጠቁመው፤ ኢትዮጵያም ከዕድሉ ተጠቃሚ እንድትሆን እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።
የአገሪቷ ተወዳዳሪ ባንኮች በሰሜን፣ በምዕራብ፣ በደቡብ እና ማዕከላዊ የአፍሪካ ቀጠና ውጤታማ የኢንቨስተመንት ስራ በማከናወን ላይ እንደሚገኙም አመላክተዋል።
ኢትዮጵያም የፋይናንስ ዘርፉን ለውጭ ኢንቨስትመንት ክፍት ለማድረግ የተለያዩ ስራዎችን ተከትሎ የሞሮኮ ባንኮች በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ከፍተኛ ፍላጎት እያሳዩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
በሞሮኮ የኢትዮጵያ ኢምባሲ የባንኮቹን ፍላጎት መሰረት በማድረግ በዘርፉ ባለው የኢንቨስትመንት አማራጭ እንዲሰማሩ ማድረግ የሚያስችል እንቅስቃሴ እደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነትን ተከትሎ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተፈጠረውን አፈር ማዳበሪያ መስተጓጎል በመሙላት ሞሮኮ ከፍተኛውን ሚና እየተወጣች እንደሆነም ተናግረዋል።
በዚህም ለኢትዮጵያ ከዓለም ገበያ ባነሰ ዋጋ እስከ 130 ሺህ ሜትሪክ ቶን የሚሆን የአፈር ማዳበሪ በማቅረብ ሞሮኮ የኢትዮጵያ ጥብቅ የንግድ አጋር መሆኗን እያሳየች እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በምግብ እራሷን ከመቻል ባለፈ ለውጪ ንግድ ለማቅረብ እያከናወነች ባለው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ላይ የሞሮኮ ድጋፍ እንዳልተለያትም ተናግረዋል።
ለዚህም ለኢትዮጵያ በሽያጭ መልክ ከምታቀርበው የአፈር ማዳበሪያ በተጨማሪ 60 ሺህ ሜትሪክ ቶን የአፈር ማዳበሪያ በድጋፍ መልክ መስጠቷን ገልጸዋል።
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ እና ሞሮኮ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ እና ማህበራዊ ዘርፎች ያላቸውን ወዳጅነት ይበልጥ ለማጠናከር እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡