የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የሚያግዝ የመምህራን አቅም ማጎልበቻ ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀቱን ገለጸ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 17 ቀን 2015 የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የሚያግዝ የመምህራን አቅም ማጎልበቻ ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀቱን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ብርሀነመስቀል ጠና ገለጹ።

 መንግስት ዩኒቨርሲቲው በትምህርት ዘርፍ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን በመደገፍ ረገድ የጀመረውን ስራ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

 የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ብርሀነመስቀል ጠና ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ አገራዊ ለውጡን ተከትሎ በትምህርት ስርዓቱ ላይ ከመዋቅር ጀምሮ ማሻሻያዎች እየተደረጉ ስለመሆናቸው ተናግረዋል። 

ለአብነትም 10ኛ ክፍል ይሰጥ የነበረው ብሔራዊ ፈተና በ12ኛ ክፍል እንዲሰጥ ከማድረግ ጀምሮ በዩኒቨርስቲዎች በ3 ዓመት ይመረቁ የነበረውን ወደ 4 ዓመት እንዲያድግ መደረጉን አስታውሰዋል። 

ባለፉት ዓመታት በተለይ በትምህርት ፍሓዊነትና ተደራሽነት ላይ በርካታ ስራ የተሰራ ቢሆንም በትምህርት አግባብነትና ጥራት ላይ አጥጋቢ ስራ ባለመሰራቱ ውጤት ሊመዘገብ አልተቻለም ብለዋል። 

ለዚህም በቅርቡ የወጣው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤት የኢትዮጵያ የትምህርት ጥራት ችግር ምን ላይ እንዳለ በግልጽ አሳይቷል ብለዋል። 

በተመሳሳይ ከዚህ ቀደም ለመምህራን ምዘና ተሰጥቶ በርካቶቹ ዝቅተኛ ውጤት ማስመዝገባቸውን አውስተው ይህ ለትምህርት ጥራት ችግሩ አይነተኛ አስተዋፆኦ እንዳለው ነው ያስረዱት። 

ለተማሪዎቹ ዝቅተኛ ውጤት መመዝገብ መምህራንን ጨምሮ አጠቃላይ የትምህርት ማህበረሰቡ ኃላፊነት ያለበት በመሆኑ ችግሩን በጋራ መፍታት ይገባል ነው ያሉት።

 መንግስት የትምህርት ዩኒቨርሲቲ አለመኖር ለትምህርት ጥራት መጓደል አንዱ ምክንያት መሆኑን በመረዳት ችግሩን ለማቃለል ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ማቋቋሙን ገልፀዋል።

 በተለያዩ ችግሮች እየተፈተነ የሚገኘውን የኢትዮጵያ የትምህርት ዘርፍ ለማከም ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ በርካታ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ አንስተዋል። 

ዩኒቨርሲቲው የመምህራንን ትምህርት ዋነኛ ምሰሶ በማድረግ የትምህርት አመራሮች፣ ተመራማሪዎች፣ አማካሪዎችና ፖሊሲ አውጪዎችን ማፍራት ላይ አተኩሮ እየሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

 በመሆኑም ዩኒቨርሲቲው የትምህርት ስብራቱን ለመጠገን የሚያስችል የመምህራን አቅም ማጎልበቻ ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀቱን ነው የተናገሩት።

 ፉኖተ ካርታው በቀጣይ ለትምህርት ሚኒስቴር እንደሚቀርብም ነው የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ብርሃነመስቀል ጠና የተናገሩት፡፡ 

መንግስት ዩኒቨርሲቲው በትምህርት ዘርፍ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን በመደገፍ ረገድ የጀመረውን ስራ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

 ሁሉም ባለድርሻ አካላት የመምህራን ሙያ በማክበርና የማስከበር ኃላፊነት እንዳለባቸው ገልፀው፤ የመምህራን እውቀትንና አቅምን ማጎልበት ደግሞ ለነገ የማይባል የዛሬ የቤት ስራ መሆኑን አመላክተዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም