የቁንዱዶ የዱር ፈረሶችን ደህንነት በመጠበቅ ለቱሪዝም መስህብ እንዲውሉ ለማስቻል እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የቁንዱዶ የዱር ፈረሶችን ደህንነት በመጠበቅ ለቱሪዝም መስህብ እንዲውሉ ለማስቻል እየተሰራ ነው

ሐረር (ኢዜአ) የካቲት 15/2015 በበኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሐረርጌ ዞን የሚገኙ የቁንዱዶ የዱር ፈረሶችን ደህንነት በመጠበቅ ለቱሪዝም መስህብና የገቢ ምንጭ እንዲውሉ ለማስቻል እየተሰራ መሆኑን የክልሉ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ።
የቁንዱዶ ፈረሶችን ዘላቂ ጥበቃን አስመልክቶ የተዘጋጀ አውደ ጥናት በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ተካሄዷል ፈረሶቹ በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ጃርሱና እና ጉርሱም ወረዳዎች መካከል 12 ሄክታር መሬት በሚያካልለው የቁንዱዶ ተራራ ላይ እንደሚገኙ ነው የተገለጸው።

ዝርያቸው ተመናምኖ ከስድስት ዓመት በፊት ስምንት ብቻ የነበሩት የቁንዱዶ የዱር ፈረሶች ከባለድርሻ አካላትና ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በተከናወነው የተቀናጀ ስራ ደህንነታቸው ተጠብቆ አሁን ላይ ቁጥራቸው 35 መድረሱን የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰይፈዲን መሃዲ ተናግረዋል።
ከባለድርሻ አካላትና ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በተከናወነው የተቀናጀ ስራ ደህንነታቸው ተጠብቆ በአሁኑ ወቅት ፈረሶቹ 35 እንደደረሱ አስታውቀዋል።

እነዚህን ሃብቶች ለቱሪዝም መስህብ በማድረግ ከዘርፉ በሚገኘውን ገቢ የአካባቢው ህብረተሰብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
አቶ ሰይፈዲን እንዳመለከቱት፤ በተለይ እንደ ኦሮሚያ ክልል ለኢኮ ቱሪዝምና ለቱሪስት የሚሆኑ ቦታዎችን ለመለየት ከተከናወኑት ውስጥ የቁንዱዶ ፈረሶች የሚገኙበት ስፍራ ይጠቀሳል።
በተለይ በምስራቅ ሐረርጌ የባቢሌ ዝሆኖች መጠለያ፣ የባቢሌ ትክል ድንጋይና የቁልቢ ገብርዔል ገዳምን ለመጎብኘት ቱሪስቶች ሲመጡ በተያያዘ የቁንደዱ ፈረሶችን እንዲመለከት ለማስተዋወቅ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
የቁንዱዶ ፈረሶችን ለቱሪዝም የገቢ ምንጭ እንዲውሉ ለማስቻል ከማህበረሰቡ ጋር በጋራ በቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝም አስረድተዋል።

የቁንዱዶ ፈረሶች ዝርያ እንዳይጠፋ ከመጠበቅ አኳያ የተከናወኑት ስራዎች አበረታችና የፈረሶቹም ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን የተናገሩት ደግሞ የኢትዮዽያ ብዝሃ ህይወት ኢንስቲዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈለቀ ወልደየስ ናቸው።
በስፍራው ከአፈር መሸርሸር፣ ከዛፎች መቆረጥና ከብቶችን ወደ ስፍራው ከማሰማራት ጋር በተያያዘ አሁንም ስጋት መኖሩን ጠቅሰዋል።
አካባቢው እንዲለማና የአካባቢው ማህበረሰብ ከዘርፉ ተጠቃሚ የሚሆንበት ሁኔታን ለማገዝ ኢንስትቲዩቱ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንትና ተመራማሪ ፕሮፌሰር መንግስቱ ኡርጌ በበኩላቸው፤' የፈረሶቹን ደህንነት በመጠበቅ ቁጥራቸው እንዲጨምርና ዩኒቨርሲቲው ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የምርምርና የተለያዩ ስራዎችን በማከናወን ፈረሶቹን ከመጥፋት መታደግ መቻሉን ተናግረዋል።
የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ ስፍራውን በአረንጓዴ የማልማት ስራ ከማከናወን ባለፈ የመንገድ፣የቱሪስት ማረፊያና ሌሎች መሰረተ ልማቶች መሟላት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የሆለታ ግብርና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተርና በቁንዱዶ ፈረሶች ላይ ጥናት ያደረጉት ዶክተር ከፈና ኢፋ የቁንዱዶ ፈረሶችን ለቱሪዝም የገቢ ምንጭ እንዲውሉ ለማስቻል የጎብኚውን እርካታ የሚያረጋግጡ የልማትና የመሰረተ ልማት ስራዎች ማከናወን ያስፈልጋል ብለዋል።
የቁንዱዶ ፈረሶች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ላይ ሰዎች እንደሰፈሩ፣ የእርሻ ሥራ እንደሚከናወን፣ ብሎም የመሠረተ ልማት ችግሮች እንዳሉ ጠቁመው፤ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት መሰራት እንዳለበት ተናግረዋል።
ማህበረሰቡም በተለይ ተራራውን ለማልማት የድርሻውን እንዲወጣ መደገፍ እንደሚገባ አመልክተዋል።
ቱሪስቱ የባቢሌ ዝሆኖች መጠለያ፣ የጀጎል ግንብ፣ የለገኦዳ የዋሻ ስዕሎችንና ሌሎች የቱሪስት ስፍራዎችን ለመጎብኘት ወደ ምስራቅ ኢትዮጵያ ሲመጣ የቁንዱዶ ፈረሶችን በማየት በዘርፉ የሚገኘው ገቢ እንዲጎለብት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል።
በምስራቅ ሐረርጌ ዞን የባቢሌ ዝሆኖች መጠለያ፣ የልጅ እያሱ አስር ቤት፣ የቁልቢ ገብርዔል ገዳም፣ የባቢሌ ትክል ድንጋይና የተለያዩ ዋሻዎች በቱሪስቶች እንደሚጎበኙ ተመልክቷል።