በጋምቤላ ክልል በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት አበረታች የልማት ስራዎች ተከናውነዋል- አቶ ኡሞድ ኡጁሉ - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ ክልል በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት አበረታች የልማት ስራዎች ተከናውነዋል- አቶ ኡሞድ ኡጁሉ

ጋምቤላ ፤ የካቲት 15 ቀን 2015(ኢዜአ) ፡- በጋምቤላ ክልል በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት አበረታች የልማት ስራዎች መከናወናቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ገለጹ።
ርዕሰ መስተዳደሩ በጋምቤላ ከተማ እየተካሄደ ባለው የክልሉ ምክር ቤት ጉባኤ ላይ ባቀረቡት ሪፖርት፤ በግማሽ የበጀት ዓመቱ በገቢ አሰባሰብ፣ በኢንቨስትመንት፣ በስራ እድል ፈጠራና በሌሎች የልማት ዘርፎች ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።
የህዝቡን ደህንነት ለማስጠበቅ በተከናወኑት ስራዎች በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች አስተማማኝ ሰላም ማረጋገጥ መቻሉን ተናግረዋል።
የክልሉን የገቢ አቅም ለማሳደግ በግማሽ በጀት በተከናወኑት ስራዎች ከ872 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን ጠቁመው፤ የተሰበሰበው ገቢ ከእቅዱ ከ61 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ እንዳለው አስታውቀዋል።

በክልሉ ባለው ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጮች ባለሃብቶችን ለመሳብ በተደረገው ጥረት በግማሽ የበጀት ዓመቱ ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 149 ባለሃብቶች በግብርና፣ በአግሮ ኢንዱስትሪና በአገልግሎት ዘርፎች ለመሰማራት ፈቃድ መውሰዳቸውን ገልጸዋል።
ፈቃድ ከወሰዱት መካከልም ለ21 ባለሃብቶች ከ10 ሺህ ሄከታር በላይ የእርሻ መሬት መሰጠቱንም ጠቁመዋል።
በክልሉ በተለያዩ ዘርፎች 12 ሺህ 200 ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር ከታቅደው በላይ ማከናወን መቻሉን አስረድተዋል።

በማህበራዊ ዘርፎችም የትምህርትና የጤና አገልገሎት ተደራሽነት ላይ እንዲሁም በግብርናውና ሌሎች ዘርፎችም አበረታች ስራዎች መከናወናቸውን ርዕስ መስተዳድሩ አብራርተዋል።
በአንፃሩ የምግብ ፍጆታዎች የዋጋ ንረት ፣ በግንባታ ግብዓቶች የዋጋ መጨመር ምክንያት የፕሮጀክቶች መጓተትና የጎርፍ አደጋ በበጀት ዓመቱ ያጋጠሙ ችግሮች መሆናቸውን በሪፖርታቸው ጠቅሰዋል።
ከምክር ቤቱ አባላት መካከል አቶ አብራሃም ማይከል በሰጡት አስተያየት፤ ጋምቤላ ከተማን ጨምሮ በሌሎችም የክልሉ አከባቢዎች የንጹህ መጠጥ ውሃና የመብራት አገልግሎትን በማዳረስ በኩል ሊሰራ እንደሚገባ አመልክተዋል።
የአዲሱ ስርዓተ ትምህርት የመማሪያ መፃህፍትን ለተማሪዎች ተደራሽ በማድረግ በኩል የሚታዩ ክፍተቶችን በቀጣይ ለማስተካከል በትኩረት መስራት እንዳለበበት የተናገሩት ደግሞ ሌለው የምክር ቤት አባል አቶ ዮናስ አበበ ናቸው።
ሌላዋ የምክር ቤት አባል ወይዘሮ ገነት ኤሊያስ ፤ ከነዳጅ ስርጭትና አቅርቦት ክፍተት ጋር በተያይዘ በትራንስፖርት ዘርፉ የሚታየው ችግር ሊስተካከል ይገባል ብለዋል።
ከምክር ቤቱ አባላት የተነሱት ጉዳዮች አግባብነት እንዳላቸውና ለማስተካከልም በቀጣይ ግማሽ የበጀት ዓመት በትኩረት የሚሰራ ይሆናል ሲሉ ርዕሰ መስተዳደሩ ገልጸዋል።
ቀጥሎ ያለው ጉባኤው በዛሬው ውሎው የክልሉን የልማትና የመልካም አስተዳደር እቅድ ክንውን ሪፖርት አዳምጦ አጽድቋል።