በሳዑዲ በሕግ ጥላ ስር የነበሩ ኢትዮጵያዊያን ወደ አገራቸው የተመለሱት ቁጥር 787 ደርሷል

86
አዲስ አበባ ግንቦት 12/2010 በሳዑዲ አረቢያ መንግሥት በሕግ ጥላ ስር የነበሩ ኢትዮጵያዊያን በምህረት ተፈትተው ወደ አገራቸው እየተመለሱ ነው። ትናንት ምሽት ከጅዳና ጅዛን የመጡ ዜጎችን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ደኤታ ዶክተር አክሊሉ ኃይለሚካኤል አቀባበል አድርገውላቸዋል። ከጅዳ 240 ኢትዮጵያዊያን ሲገቡ  450 የሚሆኑት ደግሞ ከጅዛን በሦስት በረራዎች አገራቸው መግባት ችለዋል። የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ዛሬ ባደረሰን መረጃ መሰረት እስካሁን ከእስር ተለቀው ወደ አገራቸው የተመለሱ ዜጎች ቁጥር ወደ 787 ከፍ ብሏል። በዛሬ ዕለትም ከእስር የተለቀቁ 143 ኢትዮጵያዊያን የሚገቡ ሲሆን ነገ ደግሞ በተመሳሳይ 143 ይገባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የቃል አቀባይ ጽህፈት ቤቱ መረጃ ያመለክታል። በትናንትናው ዕለት ወደአገራቸው ከገቡት መካከል ለስድስት ዓመታት በሳዑዲ አረቢያ የቆየችው ወጣት እስከዳር ክፈተው፤ በሰው አገር መኖር ከባድ መሆኑን ገልጻ ለአገሯ እንድትበቃ ላደረገው የኢትዮጵያ መንግሥት ምስጋናዋን አቅርባለች። ለረጅም ዓመት በእስር ማሳለፋቸውን የሚገልጹት ወይዘሮ ሙና ኢብራሂም ያፈሩት ሀብት ንብረት ተዘርፎ ባዶ ቢቀሩም ወደ አገራቸው በመመለሳቸው ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል። ወጣት ሀጂብ ሰማንም በሰው አገር ሁል ጊዜ መደሰት እንደሌለ ገልጾ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣቱ መደሰቱን ተናግሯል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያውያኑ በአጭር ጊዜ መለቀቃቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያደረጉት የስራ ጉብኝት ዲፕሎማሲያዊ ስኬት እንደተመዘገበበት አመላካች ነው። ኢትዮጵያዊያንኑን ለመቀበል በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሥር ጊዜያዊ ኮሚቴ መቋቋሙን ገልጸው በዚህም ዜጎች ወደ አገራቸው እንዲገቡ ዝግጅት ሲደረግ እንደነበር አስታውሰዋል። ከአገሮች ጋር የሚደረግ ግንኙነት በዜጎች ክብርና ሰብአዊ መብት ላይ የሚያተኩር እንደሆነ ቃል አቀባዩ ገልጸዋል። ከሱዳን 1ሺ 400 የሚሆኑ ስደተኞች መፈታታቸውን ያስታወሱት አቶ መለስ በኬኒያ ያሉ ዜጎችን ደግሞ ቦታውን የመለየት ዝርዝራቸውን የማወቅና የጉዞ ሰንድ የማዘጋጀት ተግባራት እየተከናወነ በመሆኑ በአጭር ጊዜ ወደ አገራቸው የሚመለሱበት ተስፋ መኖሩን ጠቁመዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም