የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የጀመረው ተግባር የስራ አጥነት ችግርን ለማቃለል የሚያስችል ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የጀመረው ተግባር የስራ አጥነት ችግርን ለማቃለል የሚያስችል ነው

ባህር ዳር፣ የካቲት 14 ቀን 2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የጀመረው ተግባር በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን የወጣት ስራ አጥነት ችግር ማቃለል የሚያስችል እንደሆነ የአማራ ክልል ስራና ስልጠና ቢሮ ገለጸ።
4ኛው ዙር የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች አንቀሳቃሾች ስልጠና በአማራ ክልል በ5 ማዕከላትና በ16 የስልጠና ጣቢያዎች ለ32 ሺህ የሚበልጡ ሰልጣኞች መሰጠት ጀምሯል።
የክልሉ ስራና ስልጠና ቢሮ ኃላፊ አቶ አረጋ ከበደ በስልጠና ማስጀመሪያው ላይ እንደገለጹት፤ ለወጣቶች የስራ ዕድል የመፍጠር ተግባር ለነገ የሚባል አይደለም።
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከለውጡ በፊት በተወሰኑ የኢኮኖሚ መስኮች ለተሰማሩ ባለሃብቶች ብድር በመስጠት ላይ ተወስኖ እንደነበር አስታውሰው፤ የብድር አገልግሎት አሰጣጡን በማሻሻል ዛሬ ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ ወደ ስራ እንዲገቡ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
ባንኩ በአሁኑ ወቅት ከፀደይ ባንክና ዋልያ የካፒታል ዕቃዎች ኢንተርፕራይዝ ጋር በመቀናጀት በክልሉ በአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ለተደራጁ አንቀሳቃሾች የብድር ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየሰራ እንደሆነ ጠቁመዋል።
ባንኩ አገልግሎቱ ተደራሽ ባልሆነባቸውና ለፈጠራ ሃሳብ ቁሳዊ ሃብት ማስያዝ ለማይችሉ ወጣቶች የጀመረው የብድር አገልግሎት የሚያበረታታና ሌሎች ባንኮችም በአርአያነት ወስደው ሊተገብሩት የሚገባ እንደሆነ አስገንዝበዋል።
በአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የተደራጁ ወጣቶችም በግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ማዕድን፣ ቱሪዝምና ሌሎች የአገልግሎት ዘርፎች በመሰማራት ራሳቸውን በመጥቀም፣ ክልላቸውንና ሀገራቸውን በኢኮኖሚ ማገዝ እንዳለባቸው ተናግረዋል።
ባንኩ ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል በክልሉ በ3 ዙሮች ከ12 ሺህ በላይ ወጣቶችን በመመልመል፣ በማሰልጠንና የብድር ተጠቃሚ በማድረግ ወደ ስራ እንዲገቡ ማድረጉን አብራርተዋል።
በዚህ ዓመትም በርካታ ወጣቶችን በመመልመል ሰልጥነው ወደ ስራ እንዲሰማሩ የጀመረው ጥረት የወጣቶችን የስራ አጥነት ችግር በፍጥነት ለማቃለል የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
ሰልጣኞች የሚሰጠውን ስልጠና በአግባቡ በመከታተል አስፈላጊውን ዕውቀትና ክህሎት ይዘው እንዲወጡም አቶ አረጋ አሳስበዋል።
በኢትዮጵያ ልማት ባንክ የባህርዳር ዲስትሪክት ስራ አስኪያጅ አቶ አንማው ገዳሙ በበኩላቸው በ4ኛው ዙር የሰልጣኞች ምልመላ በክልሉ ከ113 ሺህ በላይ ሰልጣኞች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።
ከነዚህ መካከልም ከ32 ሺህ የሚበልጡት በ5 ማዕከላት በ16 የስልጠና ጣቢያዎች ስልጠናውን ዛሬ መውሰድ እንደጀመሩ ጠቁመዋል።
ሰልጣኞቹ በ5 ቀናት ቆይታቸው በንግድ ስራ ክህሎት፣ በቢዝነስ ፕላን ዝግጅት፣ በገበያ ልማት፣ በፋይናንስ ዝግጅትና ትንተና እንዲሁም በፖሊሲ ጥናት ላይ ያተኮረ ስልጠና እንደሚሰጣቸው አስረድተዋል።
ቀሪዎቹ ተመዝጋቢዎች በቀጣይ ተከታታይ 2 ዙሮች የተዘጋጀውን ስልጠና በየማዕከላቱ እንደሚወስዱ አመልክተዋል።
የስልጠናው ተሳታፊ ወጣት ለበሰ ባዬ በሰጠው አስተያየት ከስልጠናው በቂ እውቀትና ክህሎት እንደሚገበይ ያለውን ተስፋ ገልጾ፤ ወደ ስራ ተሰማርቶ ለራሱና ለአገሩ የሚጠቅም ተግባር ለማከናወን መዘጋጀቱን ገልጿል።
ቀደም ሲል ባንኩ በ3 ዙሮች በሰጣቸው ስልጠናዎች በክልሉ ከ12 ሺህ ለሚበልጡ ሰልጣኞች ስልጠናውን በመስጠትና ብድር በማመቻቸት ወደ ስራ እንዲገቡ ማድረጉን ከባንኩ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።