በገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ የተመራ የኢትዮጵያ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ቤጂንግ ገብቷል

የካቲት 14/2015 (ኢዜአ) በኢፌዲሪ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ የተመራ የኢትዮጵያ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ቻይና ቤጂንግ መግባቱ ተገለጸ።

ልዑካን ቡድኑ በኢትዮጵያ እና ቻይና መካከል ያለውን የሁለትዮሽ የንግድ፣ የኢንቨስትመንትና ኢኮኖሚያዊ ትብብር ለማጠናከር ከቻይና የስራ ኃላፊዎች ጋር እንደሚመክር ተጠቁሟል።

ልዑካን ቡድኑ ከቻይና ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ ከፋይናንስ ተቋማት እና ከኢንቨስትመንት ኩባንያዎች ጋር ስትራቴጂካዊ ውይይት ያደርጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ነው የተገለጸው።

የልኡካን ቡድኑ በኢትዮ-ቻይና የጋራ የኢኮኖሚና ንግድ ኮሚሽን ስብሰባ ላይ እንዲሁም በቻይና የኢትዮጵያ ኤምባሲ በሚያዘጋጀው የኢትዮ-ቻይና የኢንቨስትመንት ፎረም ላይ እንደሚሳተፍ ተጠቁሟል።

ከፍተኛ የልዑካን ቡድኑ የገንዘብ ሚኒስትሩን አቶ አህመድ ሽዴን ጨምሮ የብሄራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ሌሊሴ ነሜ፣ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ኢዮብ ተካልኝ እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎችን ያካተተ መሆኑን በቻይና የኢትዮጵያ ኤምባሲ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ያሰፈረው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም