ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተወዳዳሪ የምርምር ማዕከል በመሆን የዜጎችን ህይወት እንደሚለውጥ ገለጹ

60
አዲስ አበባ ግንቦት 12/2010 በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ቄለም ወለጋ አዲስ የተከፈተው የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ በቀድሞው መሰረት ላይ በመቆም የጥናትና ምርምር ማዕከል በመሆን አገሪቷንና ሕዝቦቿን በዓለም ደረጃ ተወዳዳሪ በማድረግ የብዙዎችን ህይወት እንደሚለውጥ ያላቸውን ተስፋ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለጹ። ጠቅላይ ሚኒስተሩ ይህን ያሉት ዛሬ ከኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳና ሌሎች ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ጋር በመሆን ዩኒቨርሲቲውን መርቀው በከፈቱበት ወቅት ነው። በንግግራቸውም ''ያለንን ሃብትና የሚጎድለንን ማወቅ ለአገር ግንባታ እጅግ ጠቃሚ ነው'' ብለዋል። የዘመናዊ ትምህርትና  ስልጣኔ ፈር ቀዳጅ በሆነው ቄለም ወለጋ አካባቢ የተከፈተው ይህ ዩኒቨርሲቲ በፊት የነበረው መሰረት ላይ በመቆም፤ ጥናትና ምርምር በማካሄድ ህዝቡንና አገሪቷን በዓለም ደረጃ ተወዳዳሪ በማድረግ የበርካቶችን ህይወት መለወጥ እንደሚያስችል ገልጸዋል። ከተለያዩ ቦታዎች ተሰባስቦ በአንድ ላይ በመሆን አንዱ የሌላውን ባህልና ታሪክ እየተማማሩ መዝለቅ ተመራጭ መሆኑን ገልጸው፣ የአካባቢው ህዝብ ከሌላ አካባቢ ለሚመጡ ተማሪዎች ባህሉን ጭምር በማስተማር የደምቢዶሎ አምባሳደር ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል። ከሌላ አካባቢ የመጡ ተማሪዎች ባይተዋርነት ሊሰማቸው እንደማይገባና ከህዝቡ ጋር ተቀላቅለው፣ አካባቢው ላይ እየተመራመሩ ጥሩ ጊዜ ማሳለፍ እንዲችሉ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ በበኩላቸው የአካባቢውን ህዝብ የልማት ጥያቄ ከመመለስ ባለፈ የህዝቡንም የኑሮ ዘይቤ ለማሻሻል የሚኖረው ፋይዳ የጎላ መሆኑን  ገልጸዋል። ቄለም ድሮ የምሁራን ምንጭ ቢሆንም በመሀል ከስሞ የነበረውን የአሁኑ ትወልድ ወደቀድሞው ለመመለስ ጠንክሮ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል። የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ በአገራችን በአዳዲስ እየተገነቡ ካሉ 11 ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ ነው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም