ኮንጓዊው ሃኪም ዴኒስ ሙክዌጌና ኢራቃዊቷ ናዲያ ሙራድ የሠላም ኖቤል ተሸላሚ ሆኑ

133
አዲስ አበባ መስከረም 25/2011 የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ተወላጁ ሃኪም ዴኒስ ሙክዌጌና ኢራቃዊቷ ናዲያ ሙራድ የ2018 የሰላም ኖቤል ተሸላሚ ሆኑ። የዘንድሮው የኖቤል ሽልማት ትኩረት የወሲብ ጥቃትን በመታገል የላቀ ተግባር ለፈፀሙ የተበረከተ ነው። በጦርነት ወቅት የሚፈፀም የወሲብ ጥቃትን የመሰለ የጦር ወንጀል ተግባርን ለዓለም በማጋለጥና ፈፃሚዎቹም ተጠያቂ እንዲሆኑ ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማድረጋቸው ለሽልማት እንደበቁ ተመልክቷል። ግለሰቦቹ ከሁለት ወራት በኋላ በኖርዌይ ኦስሎ በሚከናወን ስነ-ስርዓት የአንድ ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ሽልማት እንደሚበረከትላቸው አልጀዚራ ዘግቧል። የማህፀን ሃኪም የሆኑት ዶክተር ዴኒስ ሙክዌጌ በኮንጎ የአስገድዶ መድፈር ሰለባ የሆኑ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሴቶችን ከማከም ባሻገር ተግባሩን ክፉኛ በመቃወም የታገሉ ናቸው። ኢራቃዊቷ ናዲያ ሙራድ ደግሞ በአስላማዊ አክራሪው ቡድን አይኤስ ታግታ የወሲብ ባሪያ የነበረች ሲሆን ቡድኑ አስገድዶ መድፈር ከፈፀመባቸውና በህይወት ከተረፉት ሶስት ሺህ የያዚዲ ሴት ልጆች መካከል አንዷ ነች። ናዲያ ሙራድ አሸባሪው ቡድን በያዚድ ሴቶቸ ላይ የሚፈፅመውን የወሲብ ጥቃት ለማጋለጥ ከፍተኛ ተግባር መፈፀሟ ለሽልማት እንዳበቃት ተነገሯል። በዘንድሮ የሰላም ኖቤል ሽልማት 216 ሰዎችና 115 ድርጅቶች በእጩነት መወዳደራቸው ታውቋል። ከቀረቡት እጩዎች መካከል በሶሪያ ጦርነት ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ለመታደግ የሚሰራው ባለ ነጭ ቆብ ማህበራዊ ቡድን፣ የሩሲያው ኖቫያ ጋዜጣ፣ ኤድዋርድ ስኖውደንና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽን እንደሚገኙበት አልጄዚራ በዘገባው ጠቅሷል። ያለፈው ዓመት የሰላም ኖቤል ሽልማት በዓለም አቀፍ ደረጃ የኒውክሌር ጦር መሳሪያን ለማስወገድ ለሚደረግ ጥረት የተሰጠ ሲሆን የዘንድሮው ደግሞ በጦርነት ወቅት የሚፈፀም የወሲብ ጥቃትን በመታገል ላበረከቱት አስተዋጽኦ ነው። በተለይ ኢራቃዊቷ ናዲያ ሙራድ ከፓኪስታናዊቷ የ17 ዓመቷ ማላላ ቀጥሎ ሽልማቱን ያገኘች ሁለተኛዋ ወጣት ተሸላሚ ለመሆን በቅታለች።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም