የኢንተርፕራይዞች ስልጠና ከነገ ጀምሮ ይሰጣል--የኢትዮጵያ ልማት ባንክ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 13/2015 በኢትዮጵያ ልማት ባንክ እና በአለም ባንክ ትብብር የአነስተኛ እና መካከለኛ አንቀሳቃሾች ኢንተርፕራይዞች አራተኛ ዙር የመጀመሪያው ስልጠና ከነገ ጀምሮ እንደሚሰጥ ተገለጸ።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የአነስተኛ እና መካከለኛ አንቀሳቃሾች አራተኛ ዙር ስልጠናን አስመልክቶ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥቷል።

የባንኩ ፕሬዝደንት ዶክተር ዮሀንስ አያሌው በዚሁ ወቅት እንዳሉት ለ4ኛ ዙር ስልጠና 50 ሺህ ሰዎችን ለማሰልጠን ታቅዶ 435 ሺህ ሰዎች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።

ለዚህም ከፍተኛ ዝግጅት መደረጉንና ስልጠናው በሶስት ዙሮች እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

የመጀመሪያው ዙር ስልጠና ከየካቲት 14 እስከ 18 /2015 ድረስ በ56 ከተሞች በ95 ማዕከላት እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

ለዚህም 200 አሰልጣኞች እንደሚሳተፉ ገልጸው እንደ ሀገር የተፈጠረው ንቅናቄ አበረታች መሆኑን ተናግረዋል።

ባንኩ መንግስት ቅድሚያ በሚሰጣቸው በግብርና እና በኢንዱስትሪ ዘርፎች ላይ ብድር በመስጠት ኢንቨስትመንትን እያስፋፋ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም