በክረምት ወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት 6 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ግምት ያላቸው ሥራዎች ተከናውነዋል

61
አዳማ መስከረም 25/2011 በመላው ኢትዮጵያ  በተካሄደው የክረምት ወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት 6 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር  ግምት ያላቸው ሥራዎች መከናወናቸውን የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ። በዘንድሮው የበጋ ወራት 5ነጥብ 5 ሚሊዮን ወጣቶች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባር ይሳተፋሉ ተብሏል ። ሚኒስቴሩ በ2010 የክረምት ወራት የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አገራዊ አፈፃጸምን ለመገምገምና በ2011 የበጋ ወራት ዕቅድ ላይ ለመምከር ያዘጋጀው የሁለት ቀናት የምክከር መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ ጀምሯል። የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ፍሬህይወት አያሌው እንደገለጹት በአገልግሎቱ 9 ነጥብ 3 ሚሊዮን ወጣቶች ተሳትፈዋል። ወጣቶቹ በተሳተፉባቸው 14 የሥራ መስኮች  በመንግሥትና በኅብረተሰቡ ሊወጣ የነበረውን ገንዘብ አድነዋል ። በአገልግሎቱ ከ20 ሚሊዮን በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ሚኒስትር ዴኤታዋ  አስረድተዋል። መንግሥት ለፕሮግራሙ ስኬታማነት ፋይናንስ በመመደብና ቅንጅታዊ አሰራርን በማጠናከር ክትትልና ድጋፍ ማድረጉንም ገልጸዋል። ለመርሃ ግብሩ ተግባራዊነት ልዩ ትኩረት በመስጠት ለመጀመሪያ ጊዜ ከአንድ ሺህ በላይ ወሰን ተሻጋሪ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ተሳትፈዋል ብለዋል። በሚኒስቴሩ የወጣቶች ጉዳይ ማካተት ንቅናቄና ተሳትፎ ማስፋፊያ ዳይሬክተር አቶ ማቲያስ አሰፋ በበኩላቸው በአገራዊው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ዘጠኝ ሚሊዮን ወጣቶች መሳተፋቸውን አስታውቀዋል።ዕቅዱ 13 ሚለዮን ወጣቶች ለማሳተፍ እንደነበር በመጠቆም። ዕቅዱ ሙሉ በሙሉ እንዳይሳካ ካደረጉት ችግሮች መካከል የግንዛቤ፣የቅስቀሳና ንቅናቄ ሥራዎች ባለመከናወናቸው መሆኑንም አስረድተዋል። በተለይ  በየደረጃው ያለው አመራር በወቅታዊ ሁኔታዎችና በሌሎች ተግባራት ላይ በመጠመዱ አገልግሎቱ ትኩረት ሳያገኝ መቅረቱን  ገልጸዋል። በክረምት ወራት ብቻ ሲካሄድ የነበረውን አገልግሎት በበጋ ወራት ለመቀጠል ዘንድሮው በበጋ ወራት 5 ነጥብ 5 ሚሊዮን በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በተለያዩ የልማት መስኮች እንደሚሳተፉ ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል ። በአገልግሎቱ ከተከናወኑት ዓበይት ሥራዎች መካከል ጤና፣ ትምህርት፣ግብርና፣ አደጋ ስጋትና ቅነሳ፣ደም ልገሳ፣አካባቢ ጥበቃና ደን ልማት እንዲሁም የትራፊክና የመንገድ ደህንነት ይገኙበታል ብለዋል። ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የድሬዳዋ አስተዳደር ወጣቶች ፌዴሬሽን ዋና ጸሐፊ ተስፋሚካኤል ፀጋዬ እንደተናገሩት አስተዳደሩ በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት 55 ሺህ ወጣቶችን ለማሳተፍ ታቅዶ 44ሺህ ያህል  ወጣቶችን አሳትፏል። አፈጻጸሙ በአካባቢው ካለው ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር የተሻለ የወጣቶች ተሳትፎ እንደታየበትና በተለይ የአረጋውያንን ቤት በመጠገንና በመንከባከብ፣በማጠናከሪያ ትምህርትና በሌሎችም ዘርፎች ስኬታማ ሥራዎች ተከናውነዋል ብለዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም