የፓን አፍሪካኒዝም ምክር ቤት በነፃ ንግድ ቀጣና ትግበራ እና የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚሰሩ አህጉራዊ ሁነቶችን ይከታተላል - ኢዜአ አማርኛ
የፓን አፍሪካኒዝም ምክር ቤት በነፃ ንግድ ቀጣና ትግበራ እና የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚሰሩ አህጉራዊ ሁነቶችን ይከታተላል

የካቲት 12/2015 (ኢዜአ) በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ትግበራ እና የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚሰሩ አህጉራዊ መርሐ ግብሮችን ስኬታማነት በትኩረት እንደሚከታተሉ የፓን አፍሪካኒዝም ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ፎርቹን ቻሩምቢራ ገለጹ፡፡
የፓን አፍሪካኒዝም ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ፎርቹን ቻሩምቢራ በምክር ቤቱና በሌሎች ቀጣናዊ ምክር ቤቶች የ2023 የስራ ዕቅድ እና በምግብ ዋስትና ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።
ፕሬዝዳንት ፎርቹን ቻሩምቢራ እንዳሉት፤ ምክር ቤቱ የአፍሪካ ሕብረት የሚያወጣቸውን ፖሊሲዎችና ፕርግራሞቾ ትግበራ መከታተልና የአፈፃፀም ክፍተቶችን መጠቆም ነው፡፡
የዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታና የዴሞክራሲ ባህል እንዲጎለብትም ይሰራል።
የአፍሪካዊያን ድምፅ የሚሰማባቸውን የጋራ መድረኮች ማመቻቸትና ሀሳብ የማንሸራሸር ዕድል በመፍጠር የተሰበሰቡ ምክረ ሀሳቦችን ለሕብረቱ አስፈፃሚ አካል የማቅረብ ኃላፊነት ይዞ ይሰራልም ብለዋል።
ለአብነትም በ2013 በአፍሪካ ግብርና እና ምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የተደረገውን የማላቦ ቃል ኪዳንን ጨምሮ ፖሊሲና ስትራቴጂዎች አፈፃፀም ትኩረት አድርጎ ክትትል ስለማድረጉ አንስተዋል።
በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ትግበራ እና የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚሰሩ አህጉራዊ መርሐ ግብሮች ስኬታማነት መከታተል ቀጣዩ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ገልፀዋል።
በዚህም የአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነት ሁሉም ሀገራት በኩል ተፈፃሚ እንዲሆን እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።
በ1963 የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሲቋቋም ዋናው ዓላማ ፖለቲካዊ ትብብር እንደነበር ገልፀው፣ አሁናዊ አፍሪካውያን ግን ከፖለቲካው ባለፈ በመካከላቸው ኢኮኖሚ ትስስር እንደሚያስፈልጋቸው ጠቅሰዋል።
ለዚህ ደግሞ ከቅኝ ገዥዎች አዕምሯዊ እስር ቤት ወጥተን በፖን አፍሪካዊነት እሳቤ መራመድ ይገባል ብለዋል።
በአውሮፓውያን አቆጣጠር 2004 የተቋቋመው የፖን አፍሪካ ምክር ቤት ከ52 የአፍሪካ ሕብረት አገራት የተውጣጡ 229 አባላትን ያቀፈ የሕብረቱ አካል ነው።
የአፍሪካ ሕብረት ሕግ አውጭ የሆነው ምክር ቤቱ ዋና መስሪያ ቤት መቀመጫ ደቡብ አፍሪካ ሚድራንድ ከተማ ውስጥ ነው።