ኢትዮጵያ ለአገራዊ ምክክር የሰጠችው ትኩረት ለዘላቂ ሰላምና የምጣኔ ሃብት ዕድገት ጥሩ መሰረት የሚያኖር ነው--ኮሚሽነር ባንኮሌ አዲኦይ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ለአገራዊ ምክክር የሰጠችው ትኩረት ለዘላቂ ሰላምና የምጣኔ ሃብት ዕድገት ጥሩ መሰረት የሚያኖር ነው--ኮሚሽነር ባንኮሌ አዲኦይ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 12/2015 ኢትዮጵያ ለአገራዊ ምክክር የሰጠችው ትኩረት ለዘላቂ ሰላምና የምጣኔ ሃብት ዕድገት ጥሩ መሰረት የሚያኖር መሆኑን በአፍሪካ ህብረት የፖለቲካ ጉዳዮች፣ ሰላምና ጸጥታ ኮሚሽነር ባንኮሌ አዲኦይ ተናገሩ።
በሰሜን ኢትዮጵያ ተፈጥሮ የነበረውን ችግር ለመቋጨት የተደረሰው የሰላም ስምምነት "የአፍሪካን ችግር በአፍሪካውያን መፍታት" እንደሚቻል ሁነኛ ማሳያ መሆኑንም ገልጸዋል።
ኮሚሽነር ባንኮሌ አዲኦይ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ በኢትዮጵያ ሰላም እንዲመጣ በአፍሪካ ህብረት ላይ እምነት በመጣል የተሄደበት ርቀትና የተገኘውን ውጤት አድንቀዋል።
የሰላም ስምምነቱ በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ከተፈረመ ጀምሮ አተገባበሩን በቅርበት እየተከታተሉ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ከሰላም ስምምነቱ በኋላ መሰረታዊ አገልግሎቶች ዳግም ስራ እንዲጀምሩና የሰብአዊ ድጋፍ በስፋት ተደራሽ በማድረግ የመንግስትን ቁርጠኝነት በማድነቅ የሰላም ሂደቱ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።
በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና የጋራ አገራዊ መግባባት ለመፍጠር አገራዊ የምክክር ኮሚሽን በማቋቋም እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችንም አወድሰዋል።
በመሆኑም ኢትዮጵያ ለአገራዊ ምክክር የሰጠችው ትኩረት ለዘላቂ ሰላምና የምጣኔ ሃብት ዕድገት ጥሩ መሰረት የሚያኖር መሆኑን ኮሚሽነር ባንኮሌ ገልጸዋል።
የትኛውንም ችግር በውይይትና በምክክር በመፍታት የጥይት ድምጽ የማይሰማባት አፍሪካን እውን ማድረግ ተገቢ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ለዚህም ኢትዮጵያ በሰሜን የነበረውን ችግር በመፍታት ለሰላም የሰጠችው ዋጋ ለሌሎችም ጥሩ ምሳሌ መሆኑን ጠቅሰዋል።
አፍሪካ የሚያጋጥሟትን ችግሮች በአፍሪካዊ መፍትሄ ለመቋጨት ለምታደርገው ጥረት የተቋማትን አቅም ማጠናከር አንደሚገባ በማስገንዘብ ለዚህም በገንዘብ መደገፍ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።