በአፍሪካ የቡና ግብይትን ለማዘመን ስራ ፈጣሪዎችን ማበረታታትና ለወጣቶች የስራ እድል መፍጠር እንደሚገባ አምባሳደር አልበርት ሙቻንጋ ገለጹ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 12/2015 በአፍሪካ የቡና ግብይትን ለማዘመን ስራ ፈጣሪዎችን ማበረታታትና ለወጣቶች የስራ እድል መፍጠር እንደሚገባ አምባሳደር አልበርት ሙቻንጋ ገለጹ።

የአፍሪካ ህብረት፣ የኢፌዴሪ ስራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ የአፍሪካ ኢ ትሬድ ግሩፕ እና ኢንተር አፍሪካ ቡና ድርጅት በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

በአፍሪካ ህብረት የኢኮኖሚ ልማት፣ ንግድ፣ ቱሪዝምና ማዕድን ኮሚሽነር አምባሳደር አልበርት ሙቻንጋ እንዳሉት የህብረቱ አባል ሀገራት የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣናውን ትግበራ በማፋጠን የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስራቸውን ማጎልበት አለባቸው።

በአፍሪካ ሀገራት መካከል ያለውን የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስር በማጠናከር በቀጣናው ያለውን ንግድ ማሳደግ ይገባል ብለዋል።

በመሆኑም የህብረቱ አባል ሀገራት የዘንድሮውን መሪ ሀሳብ ገቢራዊ በማድረግ የቡናን ንግድ ማሳደግና የወጣቶችን ስራ ፈጣሪነት ማበረታታት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

የኢፌዴሪ ስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ንጉሱ ጥላሁን አፍሪካ የወጣቶች ስብስብ መሆኗን እንደመልካም እድል ጠቀም እንደሚገባ ገልጸዋል።

በየዓመቱ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመርቀው የሚወጡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶችን በስራ በሙያ ክህሎት፣ ስልጠናና ፋይናንስ በመደገፍ ስራ ፈጣሪዎች ማድረግ ይገባል ብለዋል።

በኢትዮጵያ የስራ እድል ፈጠራ በመልካም ሂደት ላይ መሆኑን የገለጹት አቶ ንጉሱ፣ ሂደቱን ቀጣናዊ ለማድረግ "የአፍሪካ ወጣቶች ስብሰባን" ዛሬ ይፋ አድርገዋል።

የአፍሪካ ኢ ትሬድ ግሩኘ በቡና ልማት ላይ ለተሰማሩ ስራ ፈጣሪዎች በአገር አቀፍም ሆነ በአህጉር አቀፍ ደረጃ ውጤታማ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የአፍሪካ ኢ ትሬዴ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሙሉዓለም ስዩም በአፍሪካ በስራ ፈጠራ ላይ ለሚሰማሩ ወጣቶች የፋይናንስ፣ የስልጠናና የገበያ ትስስር ድጋፍ እናደርጋለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም