የዓለም ባንክ በ2023 ለአፍሪካ ከ50 ቢሊዮን ዶላር የማያንስ በጀት ይመድባል - ኢዜአ አማርኛ
የዓለም ባንክ በ2023 ለአፍሪካ ከ50 ቢሊዮን ዶላር የማያንስ በጀት ይመድባል

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 12/2015 የዓለም ባንክ በ2023 ለአፍሪካ ከ50 ቢሊዮን ዶላር የማያንስ በጀት እንደሚመድብ የዓለም ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት ኦስማኔ ዲያጋና ገለጹ።
በ36ተኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት የዓለም ባንክ ምክትል ፕሬዝዳንት ኦስማኒ ዲያግና ለኢዜአ እንደገለጹት፣ አፍሪካ ከምን ጊዜም በላይ ድጋፍ የሚያስፈልጋት ጊዜ አሁን ነው ብለዋል።
አፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በድርቅ፣ በምግብ ዋስትና ፣ በኮሮና ቫይረስ ተፅዕኖና በፖለቲካ አለመረጋጋት ፈተናዎች ውስጥ እንደምትገኝም ጠቅሰዋል።
ተፅዕኖው በመሪዎች በሳል የአመራር ስልትና በህዝቦች የጋራ ትብብር ብቻ እንደሚቀለበስ የጠቀሱት ምክትል ፕሬዝዳንቱ፣ ለዚህ የሚረዱ የመፍትሄ ሃሳቦችን ከአሁኑ ማመንጨት ይገባል ብለዋል።

በመሆኑም የዓለም ባንክ ችግሩን ለማቃለል ለአፍሪካ የሚያደርገው የፋይናንስ ድጋፍ በፈረንጆቹ 2022 ከነበረው በጀት ላቅ ያለ እንደሚሆን አረጋግጠዋል።
ባንኩ ከመደበኛ በጀቱ ውጪ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን የሚደግፍ መሆኑን በማንሳት የአህጉሪቷ ህዝብና መንግስት ያላቸውን ሀብት በመጠቀም ይህን ከባድ ጊዜ ማለፍ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
ባንኩ እኤአ በ2022 ለአፍሪካ 50 ቢሊዮን ዶላር በጀት መመደቡን በማስታወስ፣እኤአ በ2023 ከአምናው የሚበልጥ ወይም የማያንስ ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።
36ተኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ "የአፍሪካን አህጉራዊ የንግድ ቀጠና ትግበራን ማፋጠን" በሚል መሪ ቃል ትላንትና መካሄድ የጀመረ ሲሆን በዛሬው እለት የተለያዩ ውሳኔዎችን በማስተላለፍ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል።