አፍሪካ በፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት የቀረበው ጥያቄ ተገቢና ፍትሓዊ ነው- የተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 11/2015 አፍሪካ በፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት የቀረበው ጥያቄ ተገቢና ፍትሓዊ ነው ሲሉ የተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ተናገሩ።

በድሕረ ሁለተኛው ዓለም ጦርነት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቁልፍ ተቋም የሆነው የፀጥታው ምክር ቤት ሲመሰረት የተሳተፈችው ብቸኛዋ የአፍሪካ አገር ኢትዮጵያ መሆኗ ይታወሳል፡፡

ምክር ቤቱ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ያላቸው ከአፍሪካ ውጭ ያሉ አምስት ሀገራት መሆናቸው ደግሞ አፍሪካ ድምጽ እንዳይሰማ አድርጓል በሚል በተደጋጋሚ ሲተች ቆይቷል፡፡

በዚህም አፍሪካ ሕብረትም ሆነ የሕብረቱ አባል ሀገራት አፍሪካ በተመድ ፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት በተደጋጋሚ ሲጠይቁ ይሰማል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በዛሬው 36ኛው የአፍሪካ ሕብረት መሪዎች ጉባዔም ሆነ ከዚህ በፊት በነበሩ መድረኮች ላይ አፍሪካ በፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት ሃሳብ ማንሳታቸው ይታወሳል።

ጉባዔውን ለመታደም በአዲስ አበባ የሚገኙት የተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጎተሬዝ፤ አፍሪካ በጸጥታው ምክር ቤቱ ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት የቀረበው ጥያቄ ተገቢና ፍትሃዊ መሆኑን ለኢዜአ ገልጸዋል።

የጥያቄው ምላሽ በድርጅቱ አባል ሀገራት የሚወሰን ቢሆንም አፍሪካ ግን እንደ አህጉር ድምጿ የሚሰማበት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት መጠየቋ አግባብነት እንዳለው ነው የተናገሩት፡፡

በርካታ የሕዝብ ቁጥር፣ የተፈጥሮ ሀብት እና ለዓለም ኢኮኖሚ የጎላ አበርክቶ ያላት አፍሪካ በፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ ውክልና አለማግኘቷ ተገቢ አለመሆኑን በተደጋጋሚ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡

አሜሪካ፣ ቻይና ፣ ሩሲያ ፣ ብሪታኒያና ፈረንሳይ በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ያላቸው ቋሚ አባል አገራት ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም