በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባለፈው የመኸር ወቅት ከለማው መሬት 27 ሚሊዮን ኩንታል የሚጠጋ ምርት ተሰበሰበ

አሶሳ (ኢዜአ) የካቲት 11 ቀን 2015 በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በ2014/2015 የመኸር ወቅት ከለማው መሬት 27 ሚሊዮን ኩንታል የሚጠጋ ምርት መሰብሰቡን የክልሉ ግብርና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ አስታወቀ።

አፈጻጸሙም ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በመሬት ሽፋን በ14 በመቶ በምርት ደግሞ በ21 በመቶ መጨመሩ ተገልጿል።

በክልሉ የ2014/15 የመኸር ወቅት ምርታማነትን በማሻሻል አርሶ አደሩ ገበያ ተኮር ሰብሎችን በስፋት እንዲያለማ መሰራቱን የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ አጥናፉ ባቡር ተናግረዋል።

በዚህም አንድ ሚሊዮን ሄክታር መሬት ለማረስ ታቅዶ ከ843 ሺህ ሄክታር በላይ መከናወኑን አመልክተው፤ በቆሎ ማሽላ፣ ጤፍ፣ አኩሪ አተር፣ ለውዝና ኑግ ከለሙት ሰብሎች መካከል እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።

አጠቃላይ አፈጻጸም የእቅዱ 75 በመቶ እንደሆነ ጠቁመው፤ ከለማው መሬትም 27 ሚሊዮን ኩንታል የሚጠጋ ሰብል መሰብሰቡን አስታውቀዋል።

በክልሉ የ2014/15 መኸር ምርት ወቅት አፈጻጸም ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ሲነጻጸር በመሬት በ14 በመቶ ምርት ደግሞ በ21 በመቶ መጨመሩን አቶ አጥናፉ ገልጸዋል።

አርሶ አደሩ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥም ሆኖ የእርሻ ስራውን ለማከናወን ያደረገውን ጥረት አበረታች እንደሆነ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም