የአፍሪካ የ2023 የ2024 ዓመታዊ እድገት 4 በመቶ ሆኖ ይቀጥላል-የአፍሪካ ልማት ባንክ ግሩፕ

የካቲት 10 ቀን 2015(ኢዜአ)፡- አፍሪካ በጎርጎሮሳውያን ዘመን አቆጣጠር ከ2023 እስከ 2024 ዓመታዊ እድገቷ 4 በመቶ ሆኖ እንደሚቀጥል የአፍሪካ ልማት ባንክ ግሩፕ ተነበየ።

ባንኩ የአፍሪካ ማክሮ ኢኮኖሚ ክንውን እና ትንበያን ይፋ አድርጓል።

የአፍሪካ ምጣኔ ሃብት አለም አቀፉ የኮቪድ ወረርሽኝ ካሳደረበት ጫና በ2022 እያገገመ ቢመጣም አዝጋሚ መሆኑን በትንበያው ተመላክቷል።

የአየር ንብረት ተጽዕኖ፣ የኮቪድ 19ና የጂኦፓለቲካ ስጋት፣ ግጭትና የሰላም እጦት እንዲሁም የሩስያና ዩክሬን ጦርነት የአፍሪካ ምጣኔ ሀብት እድገትን አዝጋሚ ካደረጉት ተጽዕኖዎች ውስጥ ተዘርዝሯል።

በአህጉሪቱ የአገር ውስጥ አማካኝ ዓመታዊ ምርት (ጂዲፒ) በ2021 ከነበረበት 4 ነጥብ 8 በመቶ በ2022 ወደ 3 ነጥብ 8 ዝቅ ማለቱን አስቀምጧል።

ከተያዘው የጎርጎሮሳውያን አቆጣጠር 2023 እስከ 2024 የአፍሪካ ዓመታዊ ዕድገት 4 በመቶ ላይ ጸንቶ እንደሚቆይ ትንበያው አስቀምጧል።

ትንበያው ውጫዊና ያልተጠበቁ ክስተቶችን ለመቋቋም ቀጣይነት ያለው አፍሪካ የፖሊሲና ዓለማቀፍ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ አመላካች መሆኑ ተጠቁሟል።

እስያ 40 በመቶውን የአፍሪካ የወጪ ንግድ መዳረሻ በመሆን የአህጉሩ አስፈላጊ የገበያ መዳረሻ በማለት አስቀምጧል።

በ2022 የነበሩ ተጽዕኖዎችን ተቋቁመው በሁሉም የአፍሪካ አገራት አወንታዊ እድገት የነበረ ሲሆን የ2023/24 ትንበያም ተቀራራቢ ሆኖ እንደሚቀጥል ትንበያው አመልክቷል።

ምስራቅ አፍሪካ በ2022 ከነበረው በ2023/24 የሚኖረው እድገት ከ5 በመቶ በላይ ሆኖ እንደሚቀጥልም አመልክቷል።

በአንጻሩ ሰሜን አፍሪካ በ2022 ከነበረበት 4 ነጥብ 3 በመቶ እድገት ለውጥ ሳያመጣ እንደሚቀጥል ተገምቷል።

የአፍሪካ ቱሪዝም ጨምሮ የተፈጥሮ ሃብት በከፍተኛ ሁኔታ በማደግ ምጣኔ ሃብቱን እንደሚግፍም ትንበያው አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም