ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ የተሻለ ስኬት እያስመዘገበች ትገኛለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ የተሻለ ስኬት እያስመዘገበች ትገኛለች

የካቲት 10 ቀን 2015(ኢዜአ) ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ የተሻለ ስኬት እያስመዘገበች መሆኑን የዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ዶንግዩ ቹ ተናገሩ፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ ከግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ ጋር ተወያይተዋል፡፡
የዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ዶንግዩ ቹ በዚሁ ወቅት ኢትዮጵያ በግብርና ዘርፍ ለአፍሪካ አገራት አብነት የሚሆን ስኬት እያስመዘገበች መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ትልቅ ህዝብና ታሪክ ያላት አገር መሆኗን ገልጸው አገሪቱ በምግብ እራሷን ለመቻል የምታደርገውን ጥረት አድንቀዋል፡፡
በሚቀጥሉት ጊዜያት ኢትዮጵያ በዘርፉ የተሻለ ስኬት እንደምታስመዘግብም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያና የአፍሪካ መዲና በሆነችሁ አዲስ አበባ እና ሌሎች አካባቢዎች አየተገነቡ ያሉት ትላልቅ ፕሮጀክች የአገሪቱን እድገት በማፈጠን በኩል ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸውም ተናግረዋል።
ድርጅቱ ባለፉት ጊዜያት የኢትዮጵያን ልማት በመደገፍ አብሮ ሲሰራ ቆይቷል፤ አሁንም በተጠናከረ መልኩ በጋራ እንሰራለን ሲሉም ነው የተናገሩት፡፡
ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ የሚከሰተውን ጉዳት ለመቀነስ በአረንጓዴ አሻራ ልማት የተሻለ ስራ እያከናወነች መሆኑንም እንዲሁ፡፡
የግብርና ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ አመንቴ በበኩላቸው ከድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ጋር ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸው ድርጅቱ አሁን በተጠናከረ መልኩ ከኢትዮጵያ ጋር መስራት እንደሚፈልግ መግለጹን አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በምግብ ራስን ከመቻል ባሻገር ስንዴን ወደ ውጭ መላክ መጀመርዋን አስታውሰው፤ በቀጣይ ከስንዴ በተጨማሪ በሩዝና ሌሎች ምርቶች ትልቅ እምርታ ለማስመዝገብ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይ የበጋ መስኖ ስራዎች ይበልጥ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አብራርተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ካለው እምቅ አቅም አንጻር አሁን ላይ በመስኖ እየለማ ያለው መሬት 10 በመቶ ብቻ መሆኑን ጠቁመው በቀጣይ ይህንን ለማሻሻል እየተሰራ ነው ብለዋል።
በዚህም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተጀመረው ጥረት በመንግስትና በልማት አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
ከዚህ አኳያ ከዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት ጋር በትብብር እንሰራለን ነው ያሉት፡፡