የአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ ላይ መረባረብ ይገባል-ቋሚ ኮሚቴው

ድሬደዋ (ኢዜአ) የካቲት 9/2015 የአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት ዘመናዊ የችግኝ ጣቢያዎችን በማስፋፋት የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ ላይ መረባረብ እንደሚገባ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

የቋሚ ኮሚቴው አባላት ዛሬ በድሬዳዋ ተገኝተው የዘመናዊ የችግኝ ጣቢያ የስራ እንቅስቃሴን ተመልክተዋል።

በዚህ ወቅት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን ላሌ እንደተናገሩት በድሬዳዋ አስተዳደር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ለማሳካት እየተከናወኑ የሚገኙ አበረታች መሆናቸውን ገልጸዋል።

በተለይ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከተገነቡ ሰባት ዘመናዊ ሞዴል የችግኝ ጣቢያዎች አንዱ በሆነው የድሬዳዋ ችግኝ ጣቢያ ውስጥ እየተባዙ የሚገኙ ሀገር በቀልና ሌሎች ችግኞች አያያዝ በአርአያነት የሚጠቀሱ ናቸው ብለዋል።

መሰል ችግኝ ጣቢያዎች በመላው ሀገሪቱ እንዲስፋፉ በማድረግ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት በአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ ላይ መረባረብ እንደሚገባ አሳስበዋል።

እንደ አቶ ሰለሞን ገለፃ፤ የድሬዳዋ ችግኝ ጣቢያ ለጎረቤት ጅቡቲ ችግኞችን በማቅረብ ጭምር የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻው የቀጠናው ሀገራት የጋራ አጀንዳ የማድረግን የመንግስት ዓላማ በማሳካት ላይ ነው።

በጉብኝቱ ላይ የተሳተፉት የኢትዮጵያ የደን ልማት ዋና ዳይሬክተር አቶ ከበደ ይማም በበኩላቸው፤ በመላው ሀገሪቱ የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ እየተከናወኑ የሚገኙ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተግባራት ውጤታማ እንዲሆኑ በማገዝ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ የወንዞችን ፍሰት በመጨመር፣ የአየር ንብረት ለውጥን በመታደግ፣ የህዳሴው ግድብ የሚፈልገውን ውጤት እንዲያስገኝና የግብርና ምርታማነት እንዲጨምር በማገዝ ወሳኝ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል።

ለዘመቻው ቀጣይነትና አሁን ያለውን የሀገሪቱን 17ነጥብ 2 በመቶ የደን ሽፋን ለማሳደግ መሠረታዊ ጉዳይ ልክ እንደ ድሬደዋ ዓይነት ሞዴልና ዘመናዊ የችግኝ ጣቢያዎች ማሳደግ ላይ መረባረብ ይገባናል ብለዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደርን የምስራቅ ኢትዮጵያ የኢንደስትሪና የአገልግሎት ማዕከል የማድረግ፣ ፅዱና አረንጓዴ የለበሰች ከተማ እንድትሆን የተጀመረውን ጉዞ ለማሳካት ሞዴል ችግኝ ጣቢያው ወሳኝ ሚና እየተጫወተ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ ናቸው።

ባለፉት ሁለት ዓመታት ሞዴል ችግኝ ጣቢያው ከመቶ ሺህ በላይ ችግኞችን አዘጋጅቶ ለጅቡቲ በማቅረብ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በአረንጓዴ አሻራ የማስተሳስሩን ተግባር ለማሳካት የድርሻውን እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን የደን ልማት ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ማስረሻ ይመር በበኩላቸው በስድስት ሚሊዮን ብር በተገነባው ሞዴል ችግኝ ጣቢያ የተዘጋጁ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሀገር በቀል ችግኞች ለአረንጓዴ አሻራው ዘመቻ በመዋል ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

"ባለፈው ዓመት በተካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ብቻ ከዚህ ጣቢያ የተሰራጩ ችግኞች የፅድቀት መጠን ከ80 በመቶ በላይ መድረሱን በጥናት ተረጋግጧል" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም