በአፍሪካ ኅብረት ሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ የኅብረቱ የተለያዩ ተቋማትና አደረጃጀቶች ምርጫ ይጠበቃል

አዲስ አበባ (ኢዜአ)የካቲት8/2015 በአፍሪካ ኅብረት ሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ የኅብረቱ የተለያዩ ተቋማትና አደረጃጀቶች ምርጫ ይጠበቃል ።

42ኛው የአፍሪካ ኅብረት የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ ዛሬ በኅብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ ተጀምሯል።

በምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ የኅብረቱ አባል አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችና ተወካዮች ይሳተፋሉ።

በስብሰባው ላይ እየተሳተፉ ከሚገኙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች መካከል የሶማሊያ፣ ናይጄሪያ፣ ኮሞሮስ፣ ታንዛንያ፣ ኢስዋቲኒ፣ ሴራሊዮን፣ ኮትዲቭዋር፣ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ዚምባቡዌና ማሊ ይገኙበታል።

የምክር ቤቱ ስብሰባ የአፍሪካ ኅብረት ቋሚ ተወካዮች ኮሚቴ በጥር ወር 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ ባደረገው 45ኛ መደበኛ ስብሰባ የተወያየባቸው አጀንዳዎች ላይ ይወያያል።

ከውይይቱ በተጨማሪ በምክር ቤቱ ስብሰባ ከፍተኛ ትኩረት ከሚያገኙ ጉዳዮች መካከል በአፍሪካ ኅብረት ሥር የሚገኙ የተለያዩ ተቋማትና አደረጃጀቶች የሚካሄዱ ምርጫዎች መሆናቸውን ኅብረቱ ገልጿል።

ምክር ቤቱ የአፍሪካ ሰብአዊና የሕዝቦች መብቶች ፍርድ ቤት ሁለት ዳኞች፣ የአፍሪካ ኅብረት የፀረ-ሙስና አማካሪ ቦርድ ስድስት አባላትና ለአፍሪካ ኅብረት የአስተዳደር ጉዳዮች ችሎት ሦስት ዳኞችን ይመርጣል።

በተጨማሪም የአፍሪካ ኅብረት የውጭ ኦዲተሮች ቦርድ ለሁለት ዓመት የሚያገለግል የአንድ አባል ምርጫ እንደሚያከናውን ኅብረቱ ገልጿል።

42ኛው የአፍሪካ ኅብረት የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት እስከ ነገ ይቆያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም