በደቡብ ክልል ባለፉት ስድስት ወራት የገጠርና የከተማ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ስራዎች መከናወናቸው ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ክልል ባለፉት ስድስት ወራት የገጠርና የከተማ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ስራዎች መከናወናቸው ተገለጸ

ሀዋሳ፣ የካቲት 08 ቀን 2015 (ኢዜአ) በደቡብ ክልል ባለፉት ስድስት ወራት የገጠርና የከተማ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ርስቱ ይርዳው አስታወቁ።
ርዕሰ መስተዳድሩ ዛሬ በተጀመረው የክልሉ ምክር ቤት ስድስተኛ ዙር ሁለተኛ ዓመት የሥራ ዘመን ሶስተኛ መደበኛ ጉባዔ ላይ የክልሉ መንግስት የ2015 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት አቅርበዋል።
በሪፓርታቸው እንዳመላከቱት የክልሉ መንግሥት የህዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ለመመለስ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ አጋማሽ በተለያዩ ዘርፎች ያቀዳቸውን ተግባራት አከናውኗል።
በገጠር ልማት ዘርፍ ከተከናወኑ ዋና ዋና ስራዎች መካከል ባለፈው የመኸር እርሻ ከ1 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች ተሸፍኖ 85 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መገኘቱን ተናግረዋል።
ሆኖም በምርት ዘመኑ በአዝርእት፣ በአትክልትና ፍራፍሬ የለማ 178 ሺህ 522 ሄክታር በዝናብ እጥረት ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት በመድረሱ 8 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ወድሟል ብለዋል።

የጠፋውን ምርት በዘንድሮው የበጋ መስኖ ልማት ለማካካስ እንዲቻልም 207 ሺህ ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ እስካሁን ከ171 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈኑን ጠቁመዋል።
ዘንድሮ በበጋ ስንዴ ልማት 20 ሺህ ሄክታር ለማልማት ታቅዶ እስካሁን በተደረገው ጥረት 17 ሺህ 356 ሄክታር ታርሶ 13 ሺህ 148 ሄክታሩ በዘር ሊሸፈን መቻሉን አንስተዋል።
በክልሉ የመስኖ ልማቱን ለማስፋፋት በተሰጠው ትኩረት በበጀት ዓመቱ 1 ሺህ 598 አነስተኛ የውሃ መሳቢያ ሞተር ፓምፕ ግዥ ተፈጽሞ ለሁሉም መዋቅሮች ተሰራጭቷል ነው ያሉት።
የ42 ከፍተኛ፣ መካከለኛ አነስተኛ የመስኖ ግድብ ጥናትና ዲዛይን ስራ ተጠናቆ ወደ ግንባታ ለማሸጋገር በሂደት ላይ እንደሚገኝም አመልክተዋል።
እንዲሁም የቡናና የቅመማ ቅመም ልማቱን ለማስፋፋት በተደረገው ጥረት ውጤት መገኘቱን ጠቅሰው፤ በተለይ ባለፉት ስድስት ወራት ከ119 ሺህ ቶን በላይ የቡናና የቅመማ ቅመም ምርት ለማእከላዊ ገበያ ማቅረብ መቻሉን ገልጸዋል።
እንዲሁም ከሰብል፣ ከቁም እንስሳት እና እንስሳት ተዋጽኦ በተፈጠረው የገበያ ትስስር ከፍተኛ ገቢ መገኘቱን ገልጸዋል።
በከተማና በገጠር በስራ እድል ፈጠራ ዘርፍ በተካሄደው እንቅስቃሴም ከ461 ሺህ በላይ ስራ ፈላጊዎችን በመመዝገብ ወደ ስራ ለማሰማራት ብርቱ ጥረት መደረጉን ጠቅሰዋል።
በህብረተሰቡ ተሳትፎ፣ በልማት አጋሮችና በመንግሥት ትብብር በተከናወነው ሁሉ አቅፍ የገጠር መንገድ ተደራሽ ፕሮግራም 188 ኪሎ ሜትር ጠጠር ማልበስና ዲሽ ስራ፣ 39 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር አዲስ መንገድ ግንባታ ተከናወኖ ለአገልግሎት መብቃቱን ርእሰ መስተዳደሩ አብራርተዋል።
የ550 ኪሎ ሜትር መንገድ፣ የ24 ዘመናዊ ድልድይ፣ 164 የገጠር ውሃ ተቋማት ጥናትና ዲዛይን ስራ መጠናቀቁንም ጠቁመዋል።
በብልሽት ምክንያት አገልግሎት መስጠት ያቆሙና ከልዩ ወረዳና ከዞን አቅም በላይ የሆኑ 4 ሺህ 607 የመጠጥ ውሃ ተቋማት ጥገና በማካሄድ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ መቻሉን በሪፖርታቸው አብራርተዋል።
በመሰረታዊ የፍጆታ አቅርቦት ረገድ 28 ሺህ ኩንታል ስኳር እና ከ6 ሚሊዮን ሊትር በላይ የምግብ ዘይት ዝቅተኛ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች በተመጣጣኝ ዋጋ መሰራጨቱን አክለዋል።
በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች በህገ ወጥ መንገድ ሲጓጓዝ የነበረ ከ72 ሺህ ሊትር በላይ ቤንዚን ናፍጣ፣ 454 የቁም እንስሳት የተወረሰ ሲሆን ከዚሁ ሽያጭም ከ9 ሚሊዮን ብር በላይ ለመንግሥት ገቢ መደረጉንና በሌሎችም ዘርፎች በበጀት ዓመቱ የተከናወኑ የልማት ስራዎችን አብራርተዋል።
በአሁኑ ወቅት የምክር ቤቱ አባላት በርእሰ መስተዳድሩ በቀረቡት ሪፖርቶች ላይ ውይይት እያደረጉ ይገኛሉ።