በኢትዮጵያ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትን ለማሻሻል ከልማት አጋሮች ጋር በትብብር እየተሰራ ነው -የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር

የካቲት 07/2015 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትን ለማሻሻል ከልማት አጋሮች ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገለጸ።

በውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ሐብታሙ ኢተፋ እና በጤና ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች የተመራ ቡድን "በወተር ፎር ኦል" አማካኝነት እየተገነቡ የሚገኙ የንጹህ መጠጥ ውሃ እና የታዳሽ ኃይል ፕሮጀክቶችን በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ጊምቢቹ ወረዳ እና በደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን ሶዶ ወረዳ ጎብኝተዋል። 

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ሐብታሙ ኢተፋ፤ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትን ለሁሉም ሕብረተሰብ ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

የንጹህ መጠጥ ውሃ እና የታዳሽ ኃይል አቅርቦትን ለማሳደግ መንግሥት ከግብረ-ሰናይ ድርጅቶች እና ከልማት አጋሮች ጋር በትብብር እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸው የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ተደራሽነትን ለማሳደግ ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ የተለያዩ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ጠቁመዋል። 

በአገር አቀፍ ደረጃ በርካታ የንጹህ መጠጥ ውሃ ሽፋን እንዳለ አንስተው፤ በተያዘው ዓመት ብቻ 6 ነጥብ 3 ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎችን የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል። 

የ"ወተር ፎር ኦል" ፕሮጀክት በ239 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በጀት በንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት እና በንጽህና አጠባበቅ የልማት ሥራዎች ላይ እየሰራ እንደሚገኝ ገለጸዋል።

''ወተር ፎር ኦል'' የተሰኘው ፕሮጀከት በመንግሥትና በግል አጋር ድርጅት በጋራ የሚሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ በንጽህና አጠባበቅ እና በኃይል አቅርቦት ልማት ፕሮግራም እየሰራ ነው ብለዋል። 

የንጹህ መጠጥ ውሃ የልማት ሥራውም ከኢትዮጵያ መንግሥት እና ከህፃናት ኢንቨስትመንት ፈንድ ፋውንዴሽን በተገኘ የ239 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በጀት እየተካሄደ እንደሚገኝ አስታውቀዋል። 

የንጹህ መጠጥ ውሃ መሰረተ-ልማት ባልተዳረሰባቸው ስምንት ክልሎች ለሚገኙ ትምህርት ቤቶች፣ ጤና ተቋማት እና መንደሮች ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል። 

የጤና ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ ያለው የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ወጥ አፈጻጸም ባይኖረውም በሚካሄደው የልማት ሥራ መሻሻል እያሳየ መሆኑን ተናግረዋል። 

በሚቀጥሉት 5 ዓመታት ተግባራዊ የሚሆነው የንጽህ መጠጥ ውኃ የልማት ስራ ሲጠናቀቅም የህብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ እየተደረገ ያለውን ሥራ ያግዛል ብለዋል።

ዶክተር ደረጀ አክለውም ፕሮጀክቱ የጤና ተቋማትን የንጹህ መጠጥ ውሃ እና የኃይል አቅርቦት እጥረት ያለባቸውን የገጠር አካባቢዎች ለማሻሻል ጉልህ ፋይዳ እንደሚኖረው ተናግረዋል። 

በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ጊምቢቹ ወረዳ እና በደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን ሶዶ ወረዳ ፕሮጀክቱ ተግባራዊ እየተደረገባቸው ከሚገኙ አካባቢዎች መካከል ይገኙበታል። 

የአካባቢው ነዋሪዎችም ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ በአካባቢያቸው እና በጤና ተቋማት ውስጥ እያጋጠማቸው የሚገኘውን የንጹህ መጠጥ ውሃ እና የኃይል አቅርቦት ችግር እንደሚቀርፍላቸው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም