ኢትዮጵያ ሙሉ የሀገር ውስጥ ፍጆታዋን ሸፍና 32 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ለውጭ ገበያ የማቅረብ አቅም አላት- አምባሳደር ግርማ ብሩ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ሙሉ የሀገር ውስጥ ፍጆታዋን ሸፍና 32 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ለውጭ ገበያ የማቅረብ አቅም አላት- አምባሳደር ግርማ ብሩ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 5/2015 ኢትዮጵያ በዘንድሮው ዓመት የሀገር ውስጥ ፍጆታዋን ሸፍና 32 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ለውጭ ገበያ የማቅረብ አቅም እንዳላት ብሔራዊ የማክሮ ኢኮኖሚና የኤክስፖርት ኮሚቴ ማረጋገጡን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማክሮ ኢኮኖሚ አማካሪና የኤክስፖርት ኮሚቴው አስተባባሪ አምባሳደር ግርማ ብሩ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፤ መስከረም 29 ቀን 2015 ዓ.ም የዘንድሮውን የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በሶማሌ ክልል ባስጀመሩበት ወቅት ኢትዮጵያ ገፅታዋን የሚለውጥ አዲስ የታሪክ ምእራፍ ውስጥ እንደምትገባ ገልጸው ነበር።
ሀገሪቱ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ስንዴ ከውጭ ማስገባት ማቆሟን ጠቅሰው፤ በዚህ ዓመት በሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ወደ ውጭ በመላክ አዲስ ታሪክ እንደምትጽፍም እንዲሁ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስቀመጡት ሀገራዊ ግብ መሰረት ኢትዮጵያ በዛሬው ዕለት ስንዴን ወደ ውጭ የመላክ ተግባርን በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን በይፋ አስጀምራለች።
በመርሐግብሩ ላይ የተገኙት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማክሮ ኢኮኖሚ አማካሪና የስንዴ ኤክስፖርት ብሔራዊ ኮሚቴ አስተባባሪ አምባሳደር ግርማ ብሩ፤ የኢትዮጵያ ስንዴ ኤክስፖርት የማድረግ ሕልም በእርሳቸው እድሜ ተሳክቶ በማየታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ለረጅም ዓመታት በተረጅነት መቆየቷን ጠቅሰው፤ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ታሪኳን የሚቀይር የስንዴ ልማት ውስጥ መግባቷን ገልጸዋል።
መንግስት ስንዴን በስፋት በማምረት በአጭር ጊዜ ከውጭ የሚገባ ስንዴን በሀገር ውስጥ ምርት መተካቱን ጠቅሰዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለብሔራዊ የማክሮ ኢኮኖሚ የስንዴ ኤክስፖርት ብሔራዊ ኮሚቴ በሰጡት መመሪያ መሰረትም፤ ኢትዮጵያ በዚህ ዓመት ወደ ውጭ መላክ የምትችለውን የስንዴ ምርት መጠን እንዲጠና መደረጉን ገልጸዋል።
በዚህም የኤክስፖርት ብሔራዊ አስተባባሪ ኮሚቴው የሀገራዊ የነፍስ ወከፍ ፍጆታና የሀገሪቱን አጠቃላይ የምርት ሚዛን በማጥናት ከፍጆታ የሚተርፍ 32 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ወደ ውጭ መላክ እንደሚቻል ማረጋገጫ መስጠቱን ነው ያወሱት።

ይህንን ተከትሎም ስንዴ አምራች የሆኑ አካባቢዎች ተለይተው የኤክስፖርት ምርቱ በመሰብሰብ ላይ ነው ብለዋል።
እስከ አሁን ባለው መረጃ ሱዳንና ኬንያን ጨምሮ ለስድስት ገዥዎች ስንዴ ወደ ውጭ ለመላክ የ3 ሚሊዮን ኩንታል ውል መፈረሙን ተናግረዋል።
የረድኤትና ሌሎች የሀገር ውስጥ ድርጅቶች ከውጭ የሚገዙትን በሀገር ውስጥ እንዲተኩ በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል የ2 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኩንታል የውል ስምምነት በመፈረም ላይ መሆኑንም አስታውሰዋል።
ይህም የሎጂስቲክስና የውጭ ምንዛሬን ከማስቀረቱ ባሻገር ተጨማሪ ገቢ ማምጣቱንም ነው ያመለከቱት።
አምባሳደር ግርማ አክለውም፤ የስንዴ ኤክስፖርቱ እንዲሳካ ብሔራዊ ኮሚቴው በትኩረት እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል።