የፓኪስታን የመድኃኒት አምራች ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው ገለጹ

የካቲት 02/2015(ኢዜአ) የፓኪስታን የመድኃኒት አምራች ኩባንያዎች በዘርፉ ኢትዮጵያ ውስጥ ሙዓለነዋያቸውን ለማፍሰስ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው ገለጹ።

ፓኪስታን ኦብዘርቨር ዛሬ ይዞት በወጣው ዘገባ ኩባንያዎቹ በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንስ መስክ በመሰማራት ጥራቱን የጠበቀ መድኃኒት ለማምረት ፍላጎት እንዳላቸው አስታውቀዋል።

በፓኪስታን የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ጀማል በከር በኢስላማባድ የንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አህሳን ዛፋር ባክታዋሪ ከተመራ የመድኃኒት አምራች ኩባንያዎች ቡድን ጋር ውይይት አካሂደዋል።


በዚሁ ጊዜ የተለያዩ የፓኪስታን መድኃኒት አምራች ኩባንያዎች በዘርፉ ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት ለማድረግ ከፍተኛ ፍላጎት አሳይተዋል።

ፓኪስታን ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ጥራት ያለው መድኃኒት ኢትዮጵያ ውስጥ በማምረት በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ እንደምትችልም የአምራች ኩባንያዎቹ ተወካይ ተናግረዋል።


እሳቸው የሚመሩት የፋርማሲዩቲካል ኩባንያም 300 የተለያዩ የህይወት አድን መድኃኒቶችን በማምረት ለገበያ እንደሚያቅርብም በማሳያነት አንስተዋል።


በተመሳሳይ በኢስላማባድ እና ራዋልፒንዲ ከተሞች የሚገኘው ኩባንያ ተወካይ ኩባንያቸው ከ150 በላይ ህይወት አድን መድኃኒቶችን የሚያመርት ሲሆን በአፍሪካ በተለይም በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት መስክ ለመሰማራት ፍላጎት አለው ብለዋል።


ከመጋቢት 27 እስከ ሚያዚያ 2 ቀን 2015 ዓ.ም የፓኪስታን የቢዝነስ ልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ ያለውን የንግድ እና የኢንቨስትመንት ዕድሎችን ለመቃኘት ወደ አዲስ አበባ እንደሚመጣ ዘገባው አመልክቷል።


በፓኪስታን የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ጀማል በከር በበኩላቸው በርካታ የፓኪስታን የመድኃኒት አምራች ኩባንያዎች በዓለም ላይ መልካም ስም እንዳላቸው ገልጸዋል።


ዳሩ ግን የተቋማት ትስስር ባለመፈጠሩ በዘርፉ ለኢትዮጵያ ገበያ ተደራሽ መሆን ሳይችሉ ቀርተዋል ነው ያሉት።


በኢስላማባድ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከተከፈተ በኋላ ግን በኢትዮጵያና በፓኪስታን መካከል ተቋማዊ ትስስር መፍጠር መቻሉን አምባሳደር ጀማል ገልጸዋል።


ኢትዮጵያ 80 በመቶ የሚሆነውን የፋርማሲዩቲካል ምርቶችን ከሌሎች ሀገራት የምታስመጣ በመሆኗ የጤናው ዘርፍ ለፓኪስታን ነጋዴዎች አዋጭ ዕድሎችን እንደሚያስገኝ ለልዑካን ቡድኑ አብራርተዋል።


የኢስላማባድ የንግድ እና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አህሳን ዛፋር ባክታዋሪ በፓኪስታን እና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን የንግድና ኢኮኖሚ ግንኙነት ለማሳደግ አምባሳደር ጀማል እያደረጉ ያለውን ጥረት አድንቀዋል።


የፓኪስታን የቢዝነስ ልዑክ ወደ ኢትዮጵያ የሚያደርገው ጉዞ ከአፍሪካ ጋር የንግድና ትስስር ለመፍጠር በር ከፋች ነው ብለውታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም