በሐረሪ ክልል መሬት ወስደው ያለ በቂ ምክንያት ግንባታ ያቋረጡ 18 ባለሃብቶች ፍቃዳቸው ተሰረዘ

ሀረር የካቲት 01/2015 (ኢዜአ) በሐረሪ ክልል መሬት ወስደው ግንባታ ከጀመሩ በኋላ ያለበቂ ምክንያት ያቋረጡ 18 ባለሀብቶች ፍቃዳቸው መሰረዙን የክልሉ የኢንተርፕራይዝ እና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ገለጸ።

በሀረሪ ክልል ትላንትና በተጀመረው የ6 ወራት የስራ አፈፃፀም ግምገማ የክልሉ ኢንተርፕራይዝ እና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ የ6 ወራት ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

የክልሉ የኢንተርፕራይዝ እና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ሰሚራ ዩሱፍ በግማሽ ዓመቱ ለ3 ሺህ 64 ወጣች የስራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ ለ2 ሺህ 564 ወጣቶች የስራ እድል መፈጠሩን ገልጸዋል፡፡

1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ 25 አዳዲስ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፍቃድ እንደተሰጠም ተናግረዋል።

በሌላ በኩል መሬት ወስደው ግንባታ ከጀመሩ በኋላ ያለ በቂ ምክንያት ያቋረጡ 18 ባለሀብቶች ፍቃዳቸው መሰረዙን አስታውቀዋል፡፡

በቀረበው ሪፖርት ላይ አስትያየታቸውን የሰጡት የሀረሪ ክልል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አዩብ አህመድ ከህገ ወጥ መሬት ወረራ ጋር በተያያዘ 58 ሺህ ካሬ ሜትር መሬት ማስመለስ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

አሁንም የቁጥጥር ክፍተቶች በመኖራቸው ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

አዲሱን የከተማ መዋቅራዊ ፕላን ተከትሎ ከተማ ይሆናሉ ተብለው በታሰቡ አካባቢዎች የመሬት ወረራ እየተበራከተ በመምጣቱ በትኩረት ሊሰራ ይገባል ነው ያሉት፡፡

የክልሉ መንግስት ኮሚኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ አቶ ሄኖክ ሙሉነህ በበኩላቸው ኢኮኖሚያዊ ጫና በሚያደርሱ ነጋዴዎች ላይ የማስተካከያ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡

የሀረሪ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ አብይ አበበ በከተማ ማስዋብ ስራ ላይ አበረታች ለውጥ ቢታይም በደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ላይ ግንዛቤ ሊፈጠር ይገባል ብለዋል፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በሰጡት ማጠቃላይ ሀሳብ በክልሉ ያለውን መሬት በአግባቡ በመጠቀም ለወጣቶች ሰፊ የስራ እድል መፍጠር ይገባል ብለዋል።

በቀጣይ በክልሉ እያንዳንዱ አመራር ስራ እድል ፈጠራ ላይ በትኩረት ሊረባረብ እንደሚገባ ገልጸው በህገ-ወጥ ግንባታ ላይ መውሰድ የተጀመረው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡

የገበያ ዋጋን ለማረጋጋት በትኩረት እንደሚሰራ በመጠቆም በተለይ በዳቦ ቤቶች ላይ አስፈላጊው ክትትልና ቁጥጥር እንዲደረግ አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡

የከተማዋ ማዘጋጃ ቤት እና የከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን ቢሮ የ6 ወራት ሪፖርትም ቀርቦ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

የተጀመረው የሴክተር መስሪያ ቤቶች የ6 ወራት ግምገማ በነገው እለትም ቀጥሎ እንደሚካሄድ ተገልጿል፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም