በማቻከል ወረዳ በ30 ሄክታር መሬት ላይ የነበረውን ተምች በኬሚካል መከላከል ተቻለ

58
ደብረ ማርቆስ ግንቦት 12/2010 በምስራቅ ጎጃም ዞን ማቻከል ወረዳ በአሜሪካ መጤ ተምች ከተጠቃው ሰብል በ30 ሄክታር መሬት ላይ ያለውን ኬሚካል በመርጨት መከላከል እንደተቻለ የወረዳው ግብርና ጽፈት ቤት አስታወቀ። የጽፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ አዲሱ ካሳ ለኢዜአ እንደተናገሩት ተምቹ ባለፈው ሚያዚያ ወር መጨረሻ በወረዳው አምስት ቀበሌዎች በመስኖ ከለማው የበቆሎ ማሳ ውስጥ በ36 ሄክታር መሬት ላይ ያለውን ወሯል። ተባዩ ድንገት ቢከሰት በሚል ቀደም ሲል ለጥንቃቄ ተዘጋጅቶ የነበረን ኬሚካል በመርጨት በአሁኑ ወቅት ተምቹን መከላከል እንደተቻለም አቶ አዲሱ ተናግረዋል። ቀሪው ስድስት ሄክታር መሬት ያለውን ተምች የአካባቢው አርሶ አደር በባህላዊ መንገድ እንዲያስወግደው ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል። አቶ አዲሱ እንዳሉት፣ ተምቹ ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንዳይስፋፋም የወረዳ ግብርና ባለሙያዎችን ከሌላ የሥራ ስምሪት ነጻ በማድረግ የአርሶአደሩን ማሳ የማሰስ ሥራ እንዲሰሩ ተደርጓል። አውዳሚ ተምቹ በቀጣዩ የመኽር እርሻ ልማት ላይ ተጽዕኖ እንዳያሳድርም አርሶ አደሩ ከሚያደርገው መከላከል በተጨማሪ በቂ የኬሚካል ዝግጅት እንዲኖር ከወዲሁ እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል። የየውላ ቀበሌ አርሶ አደር ቄስ ታደሰ በላይ በበኩላቸው፣ በግማሽ ሄክታር የበቆሎ ማሳቸው ላይ የተከሰተውን ተምች ለመከላከል እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት ሩብ ሄክታሩን ኬሚካል በመርጨት መከላከል የቻሉ ሲሆን ቀሪውን በሕይወት ያለውን ተምች በእጅ ለቀማ ለማጥፋት ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል። ተምቹ አንድ ሄክታር በሚጠጋ የበቆሎ ማሳቸው ላይ ጉዳት ማድረሱን የገለጹት ደግሞ የእዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር አንለይ ልጅዓለም ናቸው። ሰሞኑን ኬሚካል በመርጨት ተባዩን የመከላከል ሥራ ሲሰሩ መቆየታቸውንና በእዚህም ሙሉ ለሙሉ ባይሆንም ለውጥ ማየት መጀመራቸውን ተናግረዋል። በወረዳው ለሰብል ልማት ምቹ የሆነ ከ41 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ ያለ ሲሆን 7 ሺህ 600 ሄክታሩ በመስኖ የሚለማ መሆኑ ታውቋል  ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም