በክልሉ በገቢ አሰባሰብ የተመዘገበውን ውጤት አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል-ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ

179

ሀረር (ኢዜአ) ጥር 30/2015 በሀረሪ ክልል በገቢ አሰባሰብ የተመዘገበውን ውጤት አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ አስገነዘቡ።

የሀረሪ ክልል መስተዳደር ምክር ቤት የ2015 በጀት አመት ስድስት ወራት የስራ አፈፃፀም ግምገማ ዛሬ ተጀምሯል፡፡

ምክር ቤቱ በዛሬው ውሎው የክልሉ ገቢዎችና የግብርና ልማት ቢሮዎችን የስራ አፈፃፀም ገምግሟል፡፡

የክልሉን የገቢዎች ቢሮ የስድስት ወራት የስራ አፈፃፀም ያቀረቡት የቢሮው ሃላፊ አቶ በቀለ ተመስገን በበጀት አመቱ በስድስት ወራት 774 ሚሊየን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 799 ሚሊየን ብር ተሰብስቧል።

የተሰበሰበው ገቢ ከ2014 በጀት አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 220 ሚሊየን ብር ጭማሪ ማሳየቱን ገልጸዋል፡፡

የክልሉ ገቢ በአግባቡ እንዳይሰበሰብ እንቅፋት በሆኑ ላይ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ጠቁመው ህገ-ወጥ ደረሰኝ ሲጠቀሙ የነበሩ የሂሳብ ባለሙያዎች ላይ እርምጃ መወሰድ መጀመሩንና ዘጠኝ የሚሆኑ ደላሎችም በህግ እንዲጠየቁ መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡

ህገ-ወጥ ደረሰኝ ሲያትም በተገኘ አንድ ማተሚያ ቤት ላይም ማተሚያ ቤቱን በማሸግ ጉዳዩ በፍርድ ሂደት ላይ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡

በሌላ በኩል በተቋሙ ዘመናዊ አሰራርን ተግባራዊ በማድረግ ለደንበኞች ጥራቱን የጠበቀ ቀልጣፋ አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የሀረሪ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በበኩላቸው ቢሮው በገቢ አሰባሰብ ያስመዘገበው ውጤት አበረታች መሆኑን ተናግረዋል።

ከዘርፉ ማግኘት የሚገባውን ገቢ ለማግኘት የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

በሌላ በኩል በክልሉ በበጀት አመቱ በግብርና ዘርፍ በስንዴ ልማት እንዲሁም በሌማት ትሩፋት መርሀ-ግብር በንብ ማነብና በከብት እርባታ ዘርፎች የተጀመሩ ስራዎችን ማስፋፋት እንደሚገባ ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል፡፡

በበጀት አመቱ ስድስት ወራት የክልሉ ገቢ ሊያድግ የቻለው በተሰራው የታክስ ማሻሻያ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የርዕሰ መስተዳድሩ የኢኮኖሚ አማካሪ አቶ ዩሱፍ ፈረጅ ናቸው።

ቢሮው የታክስ ተደራሽነቱን ሊያሰፋ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

በሌላ በኩል በግብርናው ዘርፍ በአሳ ዝርያ ስርጭትና በእንቁላል ምርት በድሬ ጠያራ ወረዳ የተጀመረው ስራ አበረታች መሆኑን የጠቆሙት አማካሪው ተሞክሮውን ወደ ተቀሩት አካባቢዎች ማስፋፋት እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

የተሻሻለ ዝርያ ያላቸውን ከብቶች ከማርባት ጋር በተያያዘ በድሬ ጠያራ ወረዳ ጥሩ ተሞክሮ ቢኖርም ተሞክሮውን ወደ ተቀሩት ወረዳች ማስፋፋት ላይ ውስንነት መኖሩን የገለፁት ደግሞ የሃረሪ ክልል ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ቢሮ ሀላፊ ወይዘሮ ሰሚራ ዩሱፍ ናቸው፡፡

በከተማው ከፍተኛ የወተት ፍላጎት በመኖሩ ተሞክሮውን ወደ ተቀሩት ወረዳዎች በማስፋፋት ምርታማነቱን ማሳደግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

የመስተዳድር ምክር ቤቱ የሴክተር መስሪያ ቤቶች የስድስት ወራት የስራ አፈፃፀም ግምገማ ነገም እንደሚቀጥል ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም