ባህላዊ ወርቅ አምራቾች ሀብታቸውን ለኢንቨስትመንት በማዋል አካባቢውን ማልማት ይጠበቅባቸዋል - ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሃሰን

186

አሶሳ (ኢዜአ) ጥር 30/2015 በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በባህላዊ መንገድ በወርቅ ማምረት የተሰማሩ ግለሰቦችና ማህበራት የሚያገኙትን ሃብት ለኢንቨስትመንት በማዋል አካባቢውን ማልማት እንዳለባቸው የክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን አስገነዘቡ።

በአሶሳ ከተማ በወርቅ ማምረትና ማቅረብ በተሰማሩ አንድ ባለሃብት የተገነባ የገበያ ማዕከል ህንጻ ዛሬ ተመርቋል።

የክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን በወቅቱ እንዳሉት ክልሉ ከሃገራዊ ለውጡ በፊት በነበረበት ጫና ህብረተሰቡ የስራ ፍላጎት እና አቅም እያለው ሃብቱን በሚገባ እንዳያለማ አድርጎታል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ህብረተሰቡ የተፈጥሮ ሃብቱን ተጠቅሞ ኑሮውን ለማሻሻል ጥረት እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የክልሉ ህብረተሰብ ከድህነት ለመውጣት የሚያደርገው ጥረት ውጤት እንዳመጣ ጠቅሰው በወርቅ ማምረትና ማቅረብ በተሰማሩ ባለሀብት ዛሬ በአሶሳ ከተማ ለምረቃ የበቃውን የገበያ ማዕከል ለአብነት ጠቅሰዋል።

ህብረተሰቡ ራሱን ከድህነት ለማውጣት የጀመረው ጥረት እንዲቀጥል መንግስት አሁን ላይ የተገኘውን ሠላም በማጠናከር ችግሮች ሲያጋጥሙም ተወያይቶ ከመፍታት ጀምሮ ምቹ ሁኔታ የመፍጠር ጥረቱን አጠናክሮ መቀጠሉን አስረድተዋል።

በተለይም በባህላዊ ወርቅ ልማት የተሰማሩ ግለሰቦችና ማህበራት የሚያገኙትን ገቢ ከማስቀመጥ ይልቅ በተለይዩ የኢንቨስትመንት መስኮች በማዋል አካባቢያቸውን ብሎም ሃገራቸውን ሊያለሙ እንደሚገባ ርዕሰ መስተዳድሩ አስገንዝበዋል።

የአሶሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አብዱልሙኒየም አብዱልዋሂድ በበኩላቸው በከተማው መሬት የወሰዱ ባለሃብቶችም በገቡት ውል መሰረት በማልማት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

በአሶሳ ከተማ በአንድ ሺህ ካሬ ሜትር መሬት ላይ ተገንብቶ ዛሬ የተመረቀው ባለ አራት ፎቅ የገበያ ማዕከል በ100ዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች የስራ እድል መፍጠሩን የገለጹት ደግሞ የባለሃብቱ ተወካይ አቶ መሃመድ ጃፈር ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም