የአውሮፓ አገራት አምባሳደሮችና የልማት አጋር አካላት የኢትዮጵያን የልማት ክንውኖች እንደሚደግፉ ገለጹ

182

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 30/2015 የተለያዩ የአውሮፓ አገራት አምባሳደሮችና አጋር አካላት የኢትዮጵያን የልማት እቅድና ክንውኖች እንደሚደግፉ ገለጹ።

የግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ፤ ከተለያዩ የአውሮፓ አገራት አምባሳደሮችና የልማት አጋሮች ጋር የኢትዮጵያን ግብርና ለመደገፍ እያደረጉት ባለው ስራ ላይ ውይይት አድርገዋል። 

ሚኒስትሩ የተወያዩት ከዴንማርክ፣ ኖርዌይ፣ ኔዘርላንድ አምባሳደሮች፣ የአውሮፓ ህብረት አምባሳደሮች፣ ከፈረንሳይ የልማት ትብብር ኤጀንሲና ሌሎች የልማት አጋሮች ጋር ነው። 

በመድረኩም አምባሳደሮቹና አጋር አካላቱ የኢትዮጵያን ልማት በመደገፍ ከዚህ በፊት ያደርጉት የነበረውን ጥረት እንደሚያጠናክሩ ገልጸዋል። 

ከኢትዮጵያ ጋር አገሮቻቸው የሚኖራቸውን የሁለትዮሽ ግንኙነት የበለጠ የማጠናከር ፍላጎት እንዳላቸው ጠቅሰው ለዚህም በትኩረት እንደሚሰሩ ነው ያረጋገጡት። 

በኢትዮጵያ በጦርነትና በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባትና ዜጎችን መልሶ ለማቋቋምም ድጋፍ እናደርጋለን ሲሉም አስታውቀው በአውሮፓ ህብረት በኩል እና ከዓለም ባንክ ጋር በመሆን የኢትዮጵያን ልማት ስራዎች በማገዝ ላይ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

በተለይም በግብርናው ዘርፍ በአነስተኛ እርሻ የሚተዳደሩ አርሶደሮችን በማገዝና ወደ ኮሜርሻላይዝድ እርሻ እንዲሸጋገሩ ለማድረግ ድጋፋችን ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት። 

የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ በበኩላቸው፤ የግብርናውን ዘርፍ ምርታማና ዘመናዊ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት የአጋሮች ድጋፍ የላቀ መሆኑን ገልጸዋል። 

በቀጣይም ትብብራቸውን በሚያጠናክሩባቸው ሁኔታዎች ላይ መወያየታቸውንና ግብርናን እንደ ቢዝነስ እና ኢንተርፕራይዝ በመውሰድ አርሶ አደሮች ውጤታማ የሚሆኑበት ስራ ቀጣይነት ይኖረዋል ብለዋል። 

አነስተኛ ማሳ ያላቸውን አርሶ አደሮች በክላስተር በማደራጀት ወደ ኢንተርፕራይዝ እንዲያድጉ ለማድረግ ፋይናንስ የማፈላለግ ስራዎች እንደሚሰሩም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም