በወልድያ ከተማ ከ39 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የውሃ ተቋማት ጥገና ተከናወነ - ኢዜአ አማርኛ
በወልድያ ከተማ ከ39 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የውሃ ተቋማት ጥገና ተከናወነ

ወልዲያ (ኢዜአ) ጥር 30/2015 በወልድያ ከተማ ከ39 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ በጦርነት የተጎዱ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተቋማት ጥገና በማከናወን ለአገልግሎት ማብቃቱን የከተማው ውሃ አገልግሎት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት የከተማዋ ነዋሪዎች በበኩላቸው በመልሶ ጥገናው ስላገኙት አገልግሎት አመስግነዋል።
የወልዲያ ከተማ ውሃ አገልግሎት ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ጌታቸው ሞገስ ለኢዜአ እንደገለጹት ባለፉት ሁለት ዓመታት በአካባቢው በነበረው ጦርነት ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የውሃ መሰረተ ልማቶች ወድመው ነበር ብለዋል።

የውሃ ተቋማቱ በመውደማቸውም የከተማው ህዝብ ከንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ጋር ተያይዞ በሚፈጠር የጤናና ሌሎች ችግሮች ሲያጋጥም እንደነበር አስታውሰዋል።
አሁን በተፈጠረው ሠላም የወደሙትን የውሃ መሰረተ ልማቶች መሳሪያዎችን በፍጥነት በመተካት የውሃ አቅርቦት ስራው መጀመሩን ተናግረዋል።
ለጥገናውም 39 ሚሊዮን 150ሺህ ብር ግምት ያላቸው የሠርፌስ፣ የጄኔሬተር፣ ሶላርና የእጅ ፓምፖች እንዲሁም የውሃ ማጠራቀሚያ ሮቶዎችና ሌሎች ቁሳቁሶች መጠገናቸውንና መተካታቸውን ገልጸዋል።

ለጥገና የዋለውን ገንዘብ ማግኘት የተቻለውም ከመንግስትና ሌሎች መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች መሆኑንም ስራ አስኪያጁ አስረድተዋል።
የውሃ ተቋማቱን ጠግኖ ለአገልግሎት ማብቃት በመቻሉም አሁን ላይ ከ120 ሺህ በላይ የሚሆነው የከተማዋ ህዝብ በግማሽ ቀን ፈረቃ የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ማግኘት ማስቻሉን አስረድተዋል።
የወልድያ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ አጸደ አማረ በሰጡት አስተያየት አሁን ላይ በግማሽ ቀን ውስጥ ፈረቃችንን ጠብቀን የመጠጥ ውሃ በማግኘታችን ተደስተናል ብለዋል።

ቀደም ሲል ከወራጅና ጉድጓድ ውሃ በመጠቀማቸው እርሳቸውን ጨምሮ ልጆቻቸው ለውሃ ወለድና ሌሎች በሽታዎች በመጋለጥ ወደ ህክምና ይመላለሱ እንደነበር ጠቁመው አሁን ይሄ ችግር በመቀረፉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የግማሽ ቀን የፈረቃ ውሃ አገልግሎቱ እንደማይዛባ የገለጹት ደግሞ ሌላው የከተማዋ ነዋሪ አቶ አምሃስላሴ ክፍሌ ናቸው።
አክለውም መንግስት እያከናወናቸው ያሉ የመሰረተ ልማቶች መልሶ ጥገና እኛም እንደ ማህበረሰብ በምንችለው ሁሉ ድጋፋችንን እንሰጣለን ብለዋል።
ለዚህም ህብረተሰቡ እኔን ጨምሮ በገንዘብና በጉልበት የድርሻችንን ለመወጣት ዝግጁ ነን ሲሉ ገልጸዋል።