የአየር ንብረትን ታሳቢ ያደረገ የእንሰሳት እርባታን በመከተል ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ያለመ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

160

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 30/2015 የአየር ንብረትን ታሳቢ ያደረገ የእንሰሳት እርባታን በመከተል ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ያለመ"ኢንቫይሮ ካው" የተሰኘ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ።

በዓለም አቀፉ የእንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩቱ (ኢልሪ) የሚካሄደው ይኸው ፕሮጀክት ለቀጣይ ሦስት ዓመታት በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ይተገበራል ተብሏል።

ፕሮጀክቱ በቢልና ሜሊንዳ ጌት ፋውንዴሽን በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ አንደሚካሄድም ተገልጿል።

ፕሮጀክቱ በዋናነት ከአየር ንብረቱ ጋር ተስማሚ የሆነ የእንስሳት እርባታ ዘዴዎችን በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ያለመ ነው።

በተጨማሪም ፕሮጀክቱ የምግብ ዋስትናን ማረጋጋጥ ዓለማው አድርጓል።

በተለይም የቁም እንሰሳት የምግብ ማብላላት ሥርዓታቸውን ተከትሎ የሚለቁትን ሚቴን የተሰኘውን ሙቀት አማቂ ጋዝ ለመቀነስ ይሰራል።

ለዚህም ደግሞ የቁም እንሰሳቱ አጠቃላይ የአመጋገብ ሥርዓታቸውንና ዝርያቸውን ማሻሻል ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ነው የተገለጸው።

የዓለም አቀፉ የእንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩቱ "የኢንቫይሮ ካው" ፕሮጀክት የኢትዮጵያ አስተባባሪ ዶክተር ሰላም መሰረት፤ ፕሮጀክቱ አካባቢ ጥበቃን ታሳቢ ያደረገ ነው ብለዋል።

በተለይም የቁም ከብቶች ሚቴን የተባለውን ሙቀት አማቂ ጋዝ ለመቀነስ የሚያስችሉ የእንስሳት ዝርያዎችን መለየትና ከአከባቢ ጋር የሚስማማ የእንስሳት ኃብት እርባታን ለማከናወን ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።

በዓለም አቀፉ የእንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩቱ የፕሮጀክቱ የፕሮጀክቱ መሪ ፕሮፌሰር ራፋይል ምሩዴ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ በእንስሳት እርባታ የተሻሻሉ አሰራሮችን በመጠቀም የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥና አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ማድረግ ይቻላል ብለዋል።

የከብትና የሰብልን ምርታማነት በመጨመር የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ እንዲቻል ማድረግ የፕሮጀክቱ ዓላማ መሆኑን ጠቁመዋል።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ ዶክተር አለማየሁ መኮንን፤ በኢትዮጵያ ያለውን የእንስሳት ኃብት እንዴት ማስተዳደር እንደሚቻል እውቀትና ልምድ የሚገኝበት ፕሮጀክት መሆኑን ገልፀዋል።

በተለይም በቁም እንሰሶች ወደ አየር የሚለቀቀውን ሚቴን የተባለውን ጋዝ ልቀት መጠን ለመቀነስ የሚያስችል ሥራዎችን ለመሥራት በሚደረገው ጥረት አጋዥ መሆኑንም ጭምር ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም