በክልሉ የሙቀቱ መጠን እየጨመረ በመምጣቱ የመንግስት የስራ ሰዓት ላይ ማሻሻያ ተደርጓል--የጋምቤላ ክልል

137

ጋምቤላ (ኢዜአ) ጥር 30/2015 በክልሉ የሙቀቱ መጠን እየጨመረ በመምጣቱ የመንግስት የስራ ሰዓት ላይ ለውጥ መደረጉን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድርና ካቢኔ ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ፒተር ሆው ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት የሙቀቱ መጠን እየጨመረ በመምጣቱና ለስራ ምቹ ባለመሆኑ ከነገ የካቲት 1 ቀን 2015 ጀምሮ ለሶስት ወራት የሚቆይ የመንግስት የስራ ሰዓት ለውጥ ተደርጓል።

በለውጡ መሰረትም በመደበኛው የስራ ሰዓት ከጧቱ 1፡00 ሰዓት እስከ 6፡30 ሰዓት የነበረው ከጠዋቱ 1፡00 ሰዓት አስከ 5፡30 እንዲሆን ተወስኗል ብለዋል።

እንዲሁም ከሰዓት በኋላ ከ9፡00 እስከ 11፡30 ሰዓት የነበረው ከ10፡00 ሰዓት እስከ 12፡0 ሰዓት እንዲሆን ተወስኗል ሲሉም አስታውቀዋል።

የስራ ሰዓት ለውጡ ወይናደጋ የአየር ጸባይ ያላቸውን የመንጌሽና የጎደሬ ወረዳዎችን እንደማይጨምር ጭምረው ገልጸዋል።

በመሆኑም የክልሉ የመንግስት ሰራተኞች በተጠቀሰው ጊዜ ወደ ቢሮ በመግባት የተለመደውን ሥራቸውን  እንዲያከናውኑ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ሜቲዮሮሎጂ ኢንስቲትዩት የጋምቤላ ክልል የሜቲዮሮሎጂ አገልግሎት ማዕከል ተወካይ አቶ ነብዩ ፈረደ በአሁኑ ወቅት የክልሉ አማካይ የቀኑ ከፍተኛ የሙቀት መጠን 42.2 ዲግሪ ሴልሺየስ መድረሱን ተናግረዋል።

እንዲሁም የሌሊቱ የሙቀት መጠን ደግሞ 14.2 ዲግሪ ሴልሺየስ መድረሱን ጠቁመው ባለፉት ወራት የቀኑ ከፍተኛ አማካኝ የሙቀት መጠን 36 እንዲሁም የለሊቱ ደግሞ 22 ዲግሪ ሴልሺየስ እንደነበር አስታውሰዋል።

በክልሉ የሞቃታማ ወራት የሚባሉት የካቲት፣ መጋቢትና ሚያዚያ ወራት ሲሆኑ በእነዚህ ወራት ውስጥ የቀኑ ከፍተኛ የሙቀት መጠን እስከ 45 ዲግሪ ሴልሺየስ የሚደርስበት ጊዜ እንዳለ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም