የወሎ ተርሸሪና ማስተማሪያ ሆስፒታል እውን እንዲሆን ለወሎ ዩኒቨርሲቲ ኃላፊነት መሰጠቱ ሥራው በጥራት እንዲከናወን ዕድል ይሰጣል--ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን

135

ደሴ (ኢዜአ) ጥር 29/2015 የወሎ ተርሸሪና ማስተማሪያ ሆስፒታል እውን እንዲሆን ለወሎ ዩኒቨርሲቲ ኃላፊነት መሰጠቱ ሥራው በጥራትና በተሻለ እንዲከናወን ዕድል ይሰጣል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገለጹ።

አቶ ደመቀ መኮንን እና የአማራ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለን ጨምሮ የፌዴራልና የክልል አመራሮችና ባለድርሻ አካላት በደሴ ከተማ የተለያዩ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችን ጎብኝተዋል። 

በጉብኝቱ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፣ ወሎ ተርሸሪና ማስተማሪያ ሆስፒታል በወሎ ህዝብና በአጋሮች ተሳትፎ ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠለት ትልቅ ፕሮጀክት መሆኑን አስታውሰዋል።

 

"ይሁን እንጂ ግንባታው በተለያዩ ምክንያቶች ተጓቶ ቆይቷል" ያሉት አቶ ደመቀ፣ "ዋናውን ሆስፒታልና የመማሪያውን ፕሮጀክት ወሎ ዩኒቨርሲቲ በሃላፊነት እንዲያሰራ መወሰኑ ሥራው በጥራትና በተሻለ እንዲከናወን ዕድል ይሰጣል" ብለዋል። 

ፕሮጀክቱ እውን እንዲሆን ገንዘብ ሚኒስቴር እና ትምህርት ሚኒስቴር ሆስፒታሉን በሀገራዊ ፕሮጀክት አካተው መያዛቸውንም አቶ ደመቀ ጠቁመዋል። 

"የሆስፒታሉ ግንባታ ከዚህ በላይ እንዳይዘገይ አስፈላጊው ድጋፍ እንዲደረግ እኛም እንጥራለን" ያሉት አቶ ደመቀ፣ የአማራ ክልልና ሌላው አካል ለግንባታው ስኬት ሚናቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል። 

የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር መንገሻ አየነ በበኩላቸው፣ "ተርሸሪና ማስተማሪያ ሆስፒታሉ እውን እንዲሆን በትኩረት እየሰራን ነው፤ የፌዴራል መንግስት የጀመረው ድጋፍም ተስፋ ሰጭ ነው" ብለዋል። 

ፕሮጀክቱ መዘግየቱ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ታግዞ በጥራትና በተሻለ ደረጃ እንዲሰራ መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥርም ገልፀዋል። 

በመጀመሪያው የግንባታ ምዕራፍ የመማሪያ ፕሮጀክቱ ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ፣ በእዚህም 10 ዘመናዊ ሕንጻዎች በመጠናቀቅ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል። 

ዋናውና በሁለተኛው ምዕራፍ የሚገነባው ተርሼሪ ሆስፒታሉ መሆኑን ጠቁመው፤ "በአጭር ጊዜ ውስጥ የግንባታ ሥራውን ለማስጀመር የጨረታ ሰነድ ተዘጋጅቷል" ብለዋል። 

ፕሮጀክቱ እውን እንዲሆን ገንዘብ ሚኒስቴርን ጨምሮ ሌሎች የፌዴራልና የክልል ተቋማትም የጀመሩትን ድጋፍ እንዲያጠናክሩ ዶክተር መንገሻ አስገንዝበዋል። 

በፌደራልና በክልሉ ከፍተኛ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ዛሬ የተጎበኙት ደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት፣ ወሎ ተርሸሪና መማሪያ ሆስፒታል፣ የደሴ መናኸሪያ እንዲሁም በግንባታ ላይ ያሉ መንገዶችና ድልድዮች ይገኙበታል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም