ኢትዮ ቴሌኮም "ኢትዮቴል ኢኖቬሽን" የተባለ አዲስ ፕሮግራም ይፋ አደረገ

380

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 29/2015 ኢትዮ ቴሌኮም ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል ሊፈጥር የሚያስችል "ኢትዮቴል ኢኖቬሽን" የተባለ አዲስ ፕሮግራም በይፋ አስጀመረ።

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ፤ በዛሬው እለት በይፋ የተጀመረው አዲስ ፕሮግራም በጀማሪ የክላውድና የሞባይል ፋይናንስ ቢዝነሶች ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።

ኩባንያው አገልግሎቱን ለማስፋትና ለማዘመን ከሚያደርገው ዘርፈ ብዙ ጥረት ባሻገር ሀገር በቀል ቴክኖሎጂዎችና ስራ ፈጠራን ለማበረታታት እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

የተቀረጸው ፕሮግራም ለጀማሪ የዲጅታልና የፋይናንስ ቴክኖሎጂ ቢዝነስንና ባለሙያዎችን የሚያበረታታ "ኢትዮቴል ኢኖቬሽን" የተባለ አዲስ ፕሮግራም መሆኑን ገልጸዋል።

ለፕሮግራሙ ስኬት ኢትዮ ቴሌኮም በቂ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ማከናወኑን የጠቀሱት ስራ አስፈፃሚዋ በዚህም በርካታ ስራዎች እንደሚሰሩ አስገንዝበዋል።

በዚሁ ፕሮግራም በመጀመሪያው ዙር ለ100 ስራ ፈጣሪ ጀማሪ የቴክኖሎጂ ካምፓኒዎች /ስታርት አፖች/ የእድሉ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ገልጸዋል።

በሁለተኛው ዙር ደግሞ ለ150 የቴክኖሎጂ ካምፓኒዎች /ስታርት አፖች/ እድሉ እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

በመሆኑም በ"ኢትዮቴል ኢኖቬሽን" ፕሮግራም የመጀመሪያው ምእራፍ መወዳደር የሚፈልጉ የክላውድና የሞባይል ፋይናንስ በኢሜል አድራሻ ማመልከት የሚችሉ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም በኤሜል አድራሻ ethiotelinnovation@ethiotelecom.et ከየካቲት 3 እስከ መጋቢት 3 ቀን 2015 ዓ.ም ማመልከት ይችላሉ ብለዋል።

የዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ለሚደረገው ጥረት ፕሮግራሙ ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ያስገነዘቡት ስራ አስፈጻሚዋ ለዚህ ፕሮግራም ስኬት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም