በደራሼ ልዩ ወረዳ የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ በሰላማዊ መንገድ እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በደራሼ ልዩ ወረዳ የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ በሰላማዊ መንገድ እየተከናወነ ነው

ጊዶሌ ጥር 29/2015 (ኢዜአ) በደቡብ ክልል ደራሼ ልዩ ወረዳ የህዝበ ውሳኔ ድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ በሰላማዊ መንገድ እየተከናወነ መሆኑን የምርጫ ማስተባበሪያ ማዕከሉ አስታወቀ።
በልዩ ወረዳው የህዝበ ውሳኔ ምርጫ ማስተባበሪያ ማዕከል አስተባባሪ አቶ እምቢያለው እናዋ ለኢዜአ እንዳስታወቁት በልዩ ወረዳው ከማለዳው 12:00 ጀምሮ የህዝበ ውሳኔው ድምጽ አሰጣጥ ሂደት በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ በመከናወን ላይ ነው።

በልዩ ወረዳው 85 የምርጫ ጣቢያዎች የሚገኙ ሲሆን 65 ሺህ 26 ነዋሪዎች ቀደም ሲል በህዝበ ውሳኔው ሊያሳትፋቸው የሚችለውን የምርጫ ካርድ የወሰዱ መሆናቸውንም አንስተዋል።
ነዋሪው የሚተዳደርበትን የክልል አወቃቀር ለመወሰን ከማለዳው ጀምሮ በነቂስ በመውጣት ድምጻቸውን እየሰጡ መሆናቸውንም አስተባባሪው አስረድተዋል።

በእያንዳንዱ የምርጫ ጣቢያዎች አምስት የምርጫ አስፈጻሚዎች ተመድበው ሥራቸውን በአግባቡ እያከናወኑና የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱን እያስኬዱ ይገኛሉ ብለዋል።
ህዝበ ውሳኔው ዴሞክራሲያዊ፣ ነፃ፣ ፍትሃዊና ታአማኒ መሆኑን የገለጹት አቶ እምቢያለው፤ የተፈቀደላቸው የሲቭክ ማህበራትና የሰብአዊ መብት ኮሚሽን አካላትም የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱን እየታዘቡ እንደሚገኙም አስተባባሪው አመልክተዋል።

በደቡብ ክልል የሚተዳደሩበትን ክልል ለመወሰን በስድስት ዞኖችና አምስት ልዩ ወረዳዎች እየተከናወነ ባለው የህዝበ ውሳኔ ድምጽ አሰጣጥ ሂደት ከ3 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ድምጻቸውን ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።