በዲላ ከተማ መራጮች በሕዝብ ውሳኔው ድምፅ እየሰጡ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በዲላ ከተማ መራጮች በሕዝብ ውሳኔው ድምፅ እየሰጡ ነው

ዲላ (ኢዜአ) ጥር 29/2015 (ኢዜአ) በጌዴኦ ዞን የዲላ ከተማ ነዋሪዎች የሚተዳደሩበት ክልል ለመወሰን እየተካሄደ በሚገኘው ሕዝበ ውሳኔ ድምጽ በመስጠት ላይ ናቸው።
በዞኑ ቡሌ ምርጫ ክልል ከሕዝበ ውሳኔው በተጨማሪ የፌዴራልና የክልል ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች አባላት ምርጫ በድጋሚ በተወሰነው መሰረት ምርጫ እየተካሄደ መሆኑን በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የዞኑ ምርጫ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት መረጃ አመልክቷል።

የምርጫ አስፈጻሚዎችና ታዛቢዎች በተገኙበ የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እየተከናወነ መሆኑን ለመታዘብ ተችሏል።
በሕዝበ ውሳኔው ድምፅ ለመስጠት ተመዝግበው የድምፅ መስጫ ካርድ የወሰዱ ነዋሪዎችም ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ ሰልፍ ይዘው ድምፅ በመስጠት ላይ ይገኛሉ።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከዞኑ ምርጫ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በጌዴኦ ዞን በተቋቋሙ በ626 የምርጫ ጣቢያዎች ከ394 ሺህ 941 በላይ ህዝብ በመራጭነት ተመዝግቦ የድምፅ መስጫ ካርድ ወስዷል።

በተጨማሪም በዞኑ ቡሌ ምርጫ ክልል ከሕዝበ ውሳኔው በተጨማሪ የፌዴራልና የክልል ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች አባላት ምርጫ በድጋሚ በተወሰነው መሰረት ምርጫ እየተካሄደ መሆኑን በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የዞኑ ምርጫ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት መረጃ አመልክቷል።

በቡሌ ምርጫ ክልል ስር በቡሌና ረጴ ወረዳዎች በተቋቋሙ 83 የምርጫ ጣቢያዎች በመራጭነት የተመዘገቡ 47 ሺህ 89 ነዋሪዎች ለሁለቱም ምክር ቤቶች አባላት ምርጫ ድምፅ እንደሚሰጡ ይጠበቃል።