ነገ በሚከናወነው የህዝበ-ውሳኔ ድምጽ አሰጣጥ ስነ-ስርዓት ላይ በንቃት ለመሳተፍ ተዘጋጅተናል--የአማሮ ኬሌ ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ነገ በሚከናወነው የህዝበ-ውሳኔ ድምጽ አሰጣጥ ስነ-ስርዓት ላይ በንቃት ለመሳተፍ ተዘጋጅተናል--የአማሮ ኬሌ ከተማ ነዋሪዎች

አማሮ ኬሌ (ኢዜአ) ጥር 28/2015 ነገ በሚከናወነው የህዝበ-ውሳኔ ድምጽ አሰጣጥ ስነ-ስርዓት ላይ በንቃት ለመሳተፍ መዘጋጀታቸውን የአማሮ ኬሌ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
በህዝበ ውሳኔው ድምጽ በመስጠት በንቃት ለመሳተፍ ነገን በጉጉት እየጠበቅን ነው ሲሉም ነዋሪዎቹ አክለዋል።
ነገ የምናካሂደው ህዝበ ውሳኔ ሠላማዊ እንዲሆን የሚጠበቅብንን ለመወጣት ተዘጋጅተናል ሲሉም ከአዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ የአማሮ ኬሌ ከተማ ነዋሪዎቹ የተናገሩት።
በደቡብ ክልል የሚተደደሩበትን የክልል አወቃቀር ለመወሰን ህዝበ ውሳኔ ከሚከናወንባቸው 11 መዋቅሮች መካከል የአማሮ ልዩ ወረዳ አንዱ ነው።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት በልዩ ወረዳው የአማሮ ኬሌ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ በረከት በዛብህ ህዝበ ውሳኔው ህዝቡ ለመጀመሪያ ጊዜ ዴሞክራሲያዊ መብቱን ተጠቅሞ የሚደራጅበትን ክልል የሚመርጥበት ሂደት መሆኑን ገልጸዋል።
ለዚህም የመራጭነት ካርድ በጊዜው ወስደን በጉጉት ስንጠባበቅ ቆይተናል ብለዋል።
የህዝበ ውሳኔ ሂደቱ ሠላማዊና እንዲሆን የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት መዘጋጀታቸውንም ተናግረዋል።
ለዚህም ሂደቱን ሊያደናቅፉ የሚችሉ ጉዳዮች እንዳይኖሩ ቀደም ብለን በየአደረጃጀታችን በመወያየት ስንሰራ ነው ቆይተናል ብለዋል ወይዘሮ በረከት።

አቶ አሸናፊ ገዝሙ የተባሉ አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው ህዝበ ውሳኔው በሰላማዊ መንገድ እንዲከናወን የማድረጉ ኃላፊነት የመንግስት አካላት ብቻ ባለመሆኑ በየአካባቢያችን ለሠላማችን ዘብ በመቆም ሠላማዊና ዴሞክራሲያው ህዝበ ውሳኔ ለማካሄድ ነገን በጉጉት እየተጠባበቅን ነው ብለዋል።

በከተማዋ እስካሁን ያለው የህዝበ ውሳኔው ቅድመ-ዝግጅት ሂደት ሠላማዊ መሆኑንና የነገውን ዕለት እየተጠባበቀ መሆኑን የተናገረው ደግሞ ወጣት ደሳለኝ ሻለቃ ነው።
ከነገ ማለዳ ጀምሮ የሚኖረው ድምፅ አሰጣጥ ሂደትም ሠላማዊ እንዲሆን ለማድረግ ከጸጥታና ደህንነት ሀይሎች ጎን በመሰለፍ የሚጠበቅብንን ሁሉ እናደርጋለን ነው ያለው።
አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች ሁሉ ከፀጥታ አካላት ጋር ተባብሮ እንደሚሰራም አረጋግጧል።
በልዩ ወረዳው ባሉት 98 የምርጫ ጣቢያዎች ከ109 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ተመዝግበው በህዝበ ውሳኔው ላይ ለመሳተፍ መዘጋጀታቸው ተጠቁሟል።
በደቡብ ክልል በነገው ዕለት በስድስት ዞኖችና አምስት ልዩ ወረዳዎች የሚተደደሩበትን የክልል አወቃቀር ለመወሰን ህዝበ ውሳኔ ድምጽ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።