ነገ ለሚካሄደው የህዝበ ውሳኔ ድምጽ አሰጣጥ አስፈላጊው ቅድመ-ዝግጅት ተጠናቋል--በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኮንሶ የምርጫ ክልል ማስተባበሪያ

ኮንሶ ካራት (ኢዜአ) ጥር 28/2015 በደቡብ ክልል ኮንሶ ዞን ነገ ለሚካሄደው የህዝበ ውሳኔ ድምጽ አሰጣጥ አስፈላጊው ቅድመ-ዝግጅት መጠናቀቁን በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኮንሶ የምርጫ ክልል ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ ሀላፊ አቶ ካይራሌ ካራሌ በተለይ ለኢዜአ እንዳሉት በምርጫ ክልሉ በሚገኙ 135 የድምጽ መስጫ ጣቢያዎች ለድምጽ መስጫ አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶች ደርሰዋል።

በእያንዳንዱ ጣቢያ የሚስጥር ድምጽ መስጫ ስፍራዎችና ለድምጽ ሰጪዎች የጸሀይ መከላከያ ዳስ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

በየጣቢያዎቹ ሶስት ምርጫ አስፈጻሚዎች መመደባቸውን የተናገሩት አቶ ካይራሌ 115 ሺህ 846 ነዋሪዎች ድምጽ ለመስጠት መመዝገባቸውንና ነገ ከማለዳ 12 ሰዓት ጀምሮ ድምፅ መስጠት እንደሚጀመር ተናግረዋል።

የኮንሶ ዞን ፖሊስ መምሪያ ሀላፊ ምክትል ኮማንደር ሰለሞን ካባይታ በበኩላቸው የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲጠናቀቅ ከክልሉ ልዩ ሀይል ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው።

በድምጽ መስጫ ጣቢያዎቹ ሰላም የሚያስከብሩ ፖሊሶች መመደባቸውንና የምርጫ ቁሳቁስ በፖሊስ ታጅቦ በየጣቢያዎቹ እንዲደርስ መደረጉን ጠቁመዋል።

የዞኑ ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ሀላፊ አቶ ጉራሽ ለሜታ እንዳሉት በዞኑ በተለያዩ አደረጃጀቶች በመታገዝ ህዝበ ውሳኔው ሰላማዊ እንዲሆን የየአካባቢውን ሚሊሻ በማሰልጠን ቅድመ-ዝግጅት ተጠናቋል።

አጠቃላይ በድምጽ አሰጣጡ ሂደት ዙሪያ መረጃ በፍጥነት መለዋወጥ እንዲቻል ለማድረግ ግብረ-ሀይል መቋቋሙን ገልጸዋል።

የኮንሶ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ገበየሁ እንዳሉት በዞኑ ነገ የገበያ ቀን በመሆኑ የድምጽ አሰጣጡ  ላይ ተጽዕኖ እንዳያስከትል ከህዝቡ ጋር በመነጋገር ገበያ ቀኑ እንዲለወጥ ስምምነት ላይ መደረሱን ገልጸዋል።

 ነገ የሚካሄደው ህዝበ-ውሳኔ ድምጽ የሚሰጠው ደቡብ ክልል በሚገኙ የኮንሶ፣ ዎላይታ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ጋሞ፣ ጌዴኦ፣ ጎፋ ዞኖች እንዲሁም በቡርጂ፣ ባስኬቶ፣ አማሮ፣ አሌ፣ ደራሼ ልዩ ወረዳዎች ላይ መሆኑን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መግለጹ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም