በጎፋ ዞን የሚካሄደው ህዝበ ውሳኔ ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲካሄድ አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል-የዞኑ ሰላምና ጸጥታ መምሪያ - ኢዜአ አማርኛ
በጎፋ ዞን የሚካሄደው ህዝበ ውሳኔ ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲካሄድ አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል-የዞኑ ሰላምና ጸጥታ መምሪያ

ጎፋ (ኢዜአ) ጥር 28/2015 በጎፋ ዞን የሚካሄደው ህዝበ ውሳኔ ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲካሄድ አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን የዞኑ ሰላምና ጸጥታ መምሪያ አስታወቀ።
የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ባደረገው የቀን ሰሌዳ መሰረት ነገ ጥር 29/2015 ዓም በስድስት ዞኖችና አምስት ልዩ ወረዳዎች ህዝበ ውሳኔ ይካሄዳል።
የዞኑ ሰላም እና ጸጥታ መምረያ ሃላፊ አቶ ብርሃኑ ጅፋሬ ለኢዜአ እንዳሉት በዞኑ ነገ የሚካሄደው ህዝበ ውሳኔ ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲካሄድ አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል።
ባለፉት ስድስት ወራት ከጸጥታ አካላት ጋር የተናበበ ዕቅድ በማውጣት ሲሰራ ቆይቷል ያሉት ሃላፊው በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫ ወቅት እና በድህረ-ምርጫ ምንም አይነት ችግር እንዳያጋጥም ተሰርቷል ነው ያሉት።
በዚህም ለጸጥታ ስጋት ሊሆኑ የሚችሉ ጉዳዮችን አስቀድሞ በመለየት ህዝበ ውሳኔውን የሚረብሽ ክስተት በየትኛውም ቀጣና እንዳይኖር ተደርጓል ብለዋል።
በህዝብ ውሳኔው ላይ የሚሳተፉ ዜጎች ምዝገባ በሰላምና በስኬት መካሄዱን አመልክተው በምርጫው ወቅትም ሰላማዊ ሂደት እንዲኖር ህዝቡ የተለመደ ትብብሩን እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
በጎፋ ዞን ባሉ 329 ምርጫ ጣቢያዎች መደበኛ ፖሊስ ተመድቦ የምርጫ ቁሳቁስ በየምርጫ ጣቢያው እንዲደርስ መደረጉንም ገልጸዋል።
ህዝበ ውሳኔው ያለምንም እንከን እንዲካሄድም ሚሊሻ እና ልዩ ሃይል አስፈላጊ በሆነበት ቦታ ድጋፍ የሚያደርጉበት አሰራር መቀመጡን ከተደረገው ዝግጅት መካከል ጠቅሰዋል።

የጎፋ ዞን ህዝበ ውሳኔ ተጠሪ አቶ ብርሃኑ ደቻሳ በበኩላቸው በዞኑ ከ304 ሺህ በላይ ዜጎች በህዝበ ውሳኔው ላይ ለመሳተፍ የሚያስችላቸውን ካርድ ወስደዋል ብለዋል።
በዞኑ በሶስት ምርጫ ማዕከላት ተከማችተው የነበሩ የምርጫ ቁሳቁሶች ወደ ሁሉም ምርጫ ጣቢያ እንደተጓጓዘም ተናግረዋል።
በብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የሰለጠኑ 1ሺህ 6መቶ 45 ምርጫ አስፈጻሚዎች በዞኑ በሚገኙ ምርጫ ጣቢያዎች እንደተሰማሩም ነው የምርጫ ተጠሪው ለኢዜአ የተናገሩት።
ከመራጩ ህዝብ ጋር ሰፊ ውይይት ተደርጓል ያሉት አቶ ብርሃኑ ህዝቡ በቂ ግንዛቤ መጨበጡን አስረድተዋል።
አሁን የሚጠበቀው ምርጫ የሚሰጥበት ቀን ብቻ ነው፤ ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ ድምጽ መስጠት አለበት ሲሉም አመልክተዋል።

በጎፋ ዞን ሳውላ ከተማ በህዝበ ውሳኔው ላይ ለመሳተፍ ካርድ ከወሰዱ ነዋሪዎች መካከል አቶ ቁምላቸው ሰለሞን በሰጡት አስተያየት ይበጀኛል የምለውን አደረጃጀት ለመምረጥ ተዘጋጅቻለሁ ብለዋል።