ለሰላም ዘብ መቆማችንን አጠናክረን እንቀጥላለን--ሼኽ ሃጂ ኢብራሒም ቱፋ - ኢዜአ አማርኛ
ለሰላም ዘብ መቆማችንን አጠናክረን እንቀጥላለን--ሼኽ ሃጂ ኢብራሒም ቱፋ

ሐረር (ኢዜአ) ጥር 28/2015 ለሰላም ዘብ መቆማችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ኘሬዚዳንት ሼኽ ሃጂ ኢብራሒም ቱፋ ገለጹ።
"አሊሞቻችን እንደሻማ ቀልጠው ያሻገሩልንን እውቀት ድልድይ ሁነን እናሻግራለን" በሚል መሪ ቃል የታላቁ ሙፍቲ ሸኸ አደም አህመድ ሀመሮን (ሼኸ አደም ቱላ) መታሰቢያ ፋውንዴሽን የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ-ግብር በሐረር ከተማ ተካሂዷል።
በገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ኘሬዚዳንት ሼኽ ሃጂ ኢብራሒም ቱፋ፣ ሙፍቲ ሸይክ አደም አህመድ ሀመሮን በሕይወት ዘመናቸው ለማህበረሰቡ ሰላምን ሲሰብኩ ቆይተዋል።
"በሰላም እና አስተምህሮት የሙፍቲ ሼክ አደም አህመድ ሀመሮንን ራዕይ ማስቀጠል ይገባል" ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ለታላቁ ሙፍቲ መታሰቢያነት ፋውንዴሽኑ ለሚያስገነባው የእውቀትና የታሪክ ማዕከል ሁሉም አሻራውን በማሳረፍ የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

"ለአንድ አገር ሰላም ሀላፊነት የመንግስትና የፀጥታ ተቋማት ብቻ ሳይሆን የማህበረሰቡ ጭምር ነው" ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ "ለሰላም ዘብ መቆማችንን አጠናክረን እንቀጥላለን" ብለዋል።
ሰላም ለእያንዳንዱ እንቅስቃሴ መሰረት በመሆኑ ሁሉም ዜጋ ከፀጥታ ተቋማት ጋር በመቆም ለአገር ሰላም የድርሻውን እንዲወጣም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የሼክ አደም ቱላ ፋውንዴሽን ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ፊላ አህመድ በበኩላቸው በሐረር ከተማ የሚገነባው ማዕከል የትምህርት አገልግሎት፣ ሙዚየም፣ ቤተ-መጻህፍ፣ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ማከናወኛ ስፍራ፣ የስብሰባ አዳራሾችና ሌሎች አገልግሎቶችን ያካተተ መሆኑን ገልፀዋል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሃር፣ ከተማ አስተዳዳሩ ለማዕከሉ ግንባታ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋገጥዋል።
የሐረሪ ክልል መንግስት ለማዕከሉ ግንባታ የሚውል መሬት ለመስጠት ቃል መግባቱም በመርሃ ግብሩ ላይ ተገልጿል።

ከሀገሪቱ ታላላቅ ዓሊሞች በቀዳሚነት የሚጠቀሱት ታላቁ ዓሊም ሙፍቲ ሸይኽ አደም ቱላ በ110 ዓመታቸው ባለፈው ጥቅምት ወር 2015 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው የሚታወስ ነው።
ሼህ አደም ቱላ ከ80 ዓመት በላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎችን በየዓመቱ አስተምረውና አንጸው በማስመረቅ የእስልምና እውቀት እንዲስፋፋ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጋቸው ተገልጿል።
ሼህ አደም ቱላ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤትን ከመሰረቱት ዑለሞች መካከል የነበሩ ሲሆን በሐረሪ ክልል ሰላምን በማስተማር በክልሉ ለሰፈነው ሰላምና መረጋጋት ሚናቸው ከፍተኛ ነበረም ተብሏል።
በሐረር ከተማ በሚገኘው ኢማም አህመድ እስታድየም ለፋውንዴሽኑ ገቢ ማሰባሰቢያ ዛሬ በተዘጋጀ መርሃ- ግብር ላይ 40 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ከእምነቱ ተከታዮች መሰብሰቡ ከአስተባባሪ ኮሚቴው ለማወቅ ተችሏል።