በደቡብ ኦሞ በነገው ዕለት ለሚካሄደው ህዝበ ውሳኔ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ተጠናቋል--የዞኑ አስተዳደር

ጂንካ (ኢዜአ) ጥር 28/2015 በነገው ዕለት ለሚካሄደው ህዝበ ውሳኔ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን የደቡብ ኦሞ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ንጋቱ ዳንሳ አስታወቁ።

በደቡብ ኦሞ ዞን ለህዝበ ውሳኔው ድምፅ መስጫ በተዘጋጁ 428 የምርጫ ጣቢያዎች የምርጫ ቁሳቁሶች መሟላታቸውም ተገልጿል።

የደቡብ ኦሞ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ንጋቱ ዳንሳ የህዝበ ውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ቅድመ ዝግጅት በተመለከተ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለፁት በዞኑ በነገው ዕለት ለሚካሄደው ህዝበ ውሳኔ አስፈላጊው ቅድመ-ዝግጅት ተጠናቋል።

በዞኑ ከ301 ሺህ በላይ መራጮች ድምፅ ለመስጠ መመዝገባቸውን ያነሱት ዋና አስተዳዳሪው ህዝበ ውሳኔውን ለማስፈፀም በተቋቋሙ ጣቢያዎች በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን ነው የተናገሩት።

ለህዝበ ውሳኔው ድምፅ መስጫ በተዘጋጁ ሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች የምርጫ ቁሳቁሶች መሟላታቸውንም ጠቁመዋል።

ህዝበ ውሳኔው ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲካሄድ በቂ ዝግጅት መደረጉን ጠቅሰው ህብረተሰቡም መብቱን ለመጠቀም በነቂስ ወጥቶ መሳተፍ እንዳለበት ጠይቀዋል።

በህዝበ ውሳኔው ላይ ድምጽ ለመስጠት የተመዘገበ ነዋሪ የሚሰጠው ድምጽ ወሳኝነት እንዳለው ገልፀው ህብረተሰቡ በህዝበ ውሳኔው ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግም ጠይቀዋል ።

በሁሉም የዞኑ አካባቢዎች የህዝበ ውሳኔው ሂደት ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲከናወን የጸጥታ ሀይሎች መሰማራታቸውንም ዋና አስተዳዳሪው አስረድተዋል።

ኢዜአ በጂንካ ከተማ በሚገኙ ድምፅ መስጫ ጣቢያዎች ተዟዙሮ ባደረገው ምልከታ በምርጫ ጣቢያዎች ለፀሐይና ለዝናብ መከላከያ የሚሆኑ መጠለያዎች እና የምርጫ ቁሳቁሶች መድረሳቸውን አረጋግጧል።

በነገው ዕለት በስድስት ዞኖችና በአምስት ልዩ ወረዳዎች ላይ የሚከናወነው የህዝበ ውሳኔ ድምጽ የመስጠት ስነ-ስርዓት ድመጽ ሰሺዎቹ የሚተዳደሩበትን የክልል አወቃቀር ለመወሰን የሚካሄድ መሆኑ ይታወሳል።

በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል ሥር በሚገኙ ኮንሶ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ወላይታ፣ ጋሞ፣ ጌዴኦና ጎፋ ዞኖች እንዲሁም ቡርጂ፣ ባስኬቶ፣ አሌ፣ አማሮና ደራሼ ልዩ ወረዳዎች ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም የሕዝበ- ውሳኔ የድምፅ አሰጣጥ የሚከናወን መሆኑን የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ማሳወቁ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም