በኢኮኖሚው ዘርፍ የተመዘገቡ ስኬቶችን በሌሎችም ዘርፎች በመድገም ሁለንተናዊ ብልጽግናን ማረጋገጥ ይገባል - አቶ አደም ፋራህ

168

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 27/2015 በኢትዮጵያ በኢኮኖሚው ዘርፍ የተመዘገቡ ስኬቶችን በሌሎችም ዘርፎች በመድገም ሁለንተናዊ ብልጽግናን ማረጋገጥ እንደሚገባ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ገለጹ።

የብልጽግና ፓርቲን ወክለው የተመረጡት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትና የፓርቲው ዋና ጽህፈት ቤት አመራሮች በፌደራል መንግስት የአስፈፃሚ አካላት የ2015 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት የአፈፃፀም ዙሪያ ውይይት አድርገዋል፡፡

የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ፤ ውይይቱ በምርጫ ወቅት ፓርቲው በፕሮግራሙ ያስቀመጣቸውና ለህዝብ ቃል የገባቸው ጉዳዮችን በመገምገም በቀጣይም አፈፃፀሙን ለማሳደግ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ብለዋል፡፡

ብልጽግና ፓርቲ ችግሮችን ቀድሞ መመከት የሚያስችል አቅም መፍጠር መቻሉን የገለጹት ምክትል ፕሬዘዳንቱ ፈተናዎች ሲያጋጥሙም ወደ መልካም እድል መቀየር እንደሚችል አሳይቷል ብለዋል፡፡

በዚህም የስራ ዕድል በመፍጠር፣ የውጭ ንግድን በማሳደግ እንዲሁም በኢኮኖሚው ዘርፍ ሁለንተናዊ ብልጽግናን የሚያረጋግጡ በርካታ ስኬቶች ተመዝግበዋል ብለዋል፡፡

የብልጽግና ፓርቲ አባላትም አራቱ "መ" ዎች ማለትም "መሳተፍ፣ መደገፍ፣ መረዳት እና መተግበር" የሚሉትን በመፈጸም በሁሉም ተቋማት ለውጥ ለማምጣት መረባረብ አለባቸው ብለዋል፡፡

የ22ቱን የፌደራል መንግስት አስፈፃሚ ተቋማት ሪፖርት ያቀረቡት የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ፤ በ2014 በጀት ዓመት የተመዘገበው 6 ነጥብ 4 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት ዘንድሮ ወደ 7 ነጥብ 5 በመቶ ከፍ እንደሚል ይጠበቃል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ባለፈው የበጀት ዓመት በተለያዩ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች እንዲሁም ዓለም አቀፍ ተፅዕኖዎች ውስጥ ሆና ያስመዘገበችው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት የሆነው ግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ማኑፋክቸሪንግና የአገልግሎት ዘርፉ ተመጋጋቢ ሆነው ኢኮኖሚውን ይመራሉ ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ታምርት መርሃ ግብር 459 የተዘጉ ኢንዱስትሪዎች መካከል 200 ውን ወደ ምርት በማስገባት ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት ተችሏልም ነው ያሉት።

አምስት አዳዲስ የምርት አይነቶችን ወደ ዓለም ገበያ ለማቅረብ ታቅዶ የተቆላና የተፈተገ ሰሊጥና የቢራ ብቅልን ጨምሮ ስድስት ምርቶችን ለውጭ ገበያ በማቅረብ 7 ነጥብ 58 ሚሊዬን ዶላር ገቢ ተገኝቷል ብለዋል፡፡

በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብርም በወተት ምርት፣ በዶሮ ስጋና እንቁላል፣ በከተማ ግብርና በአትክልትና ፍራፍሬ ምርት አመርቂ ውጤቶች ተመዝግቧል ብለዋል።

የዓለም አቀፉ ነባራዊ ሁኔታ እንዳለ ሆኖ የሀገር ውስጥ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ፣ ኮንትሮባንድ፣ ሙስና እና ብልሹ አሰራር የማክሮ ኢኮኖሚው እንቅፋት እንዳይሆኑ መስራት ይገባል ነው ያሉት።

በ2015 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት ከወጭ ንግድ 2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ 1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር በማግኘት ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ7 በመቶ ያነሰ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት ስድስት ወራት ከማዕድን ምርት የተገኘው የውጭ ምንዛሬ 35 ነጥብ 9 በመቶ ብቻ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ፤ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 56 ነጥብ 6 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል ብለዋል፡፡

የብልፅግና ፓርቲ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በበኩላቸው መንግስት በግብርና፣ ማኑፋክቸሪንግና ማዕድን ዘርፍ ያሉ ማነቆዎችን በመፍታት የማክሮ ኢኮኖሚውን ማሳደግ እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

የማዕድን ዘርፍ በተለይም የወርቅ ምርት በአግባቡ ቁጥጥር ካልተደረገበት ለኢትዮጵያ የምግብ ዋስትና ብቻ ሳይሆን የብሔራዊ ስጋትም ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

በመሆኑም መንግስት ህግ በማስከበር የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርግ አሰራር መዘርጋትና ኢኮኖሚውን ማሳደግ አለበት ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በማሳደግ የዜጎችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ መንግስት ግብርናውን በማዘመን ምርትና ምርታማነት ማሳደግ ላይ ማተኮር እንዳለበትም ገልጸዋል።

ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የግብርና ምርቶችን በማምረትና ለአርሶ አደሩ የገበያ ትስስር በመፍጠር ዘርፉን ማሳደግ ይገባልም ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም