የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤውን ነገ ማካሄድ ይጀምራል

224

ድሬዳዋ( ኢዜአ) ጥር 26/2015 የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት 3ተኛ የሥራ ዘመን ሁለተኛ ዓመት 4ተኛ መደበኛ ጉባኤውን ለሁለት ቀናት እንደሚያካሂድ የምክር ቤቱ አፈጉባኤ ወይዘሮ ፈትህያ አደን ተናገሩ።

አፈ ጉባኤዋ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ነገ የሚጀምረው መደበኛ ጉባኤ የአስፈጻሚ አካሉን የስድስት ወራት የልማትና የመልካም አስተዳደር ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርትን ይገመግማል።

በተለይ በገጠር እና በከተማው የተከናወኑ የልማት፣ የመልካም አስተዳደር እንዲሁም ፍትሃዊና ፈጣን ፍትህ ለመስጠት የተሰሩ ስራዎችን ይገመግማል።

በተጨማሪም በአስተዳደሩ 10 ተቋማት ላይ የተጀመሩ የሪፎርም ተግባራት፣ በአገርና በድሬዳዋ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የተከናወኑ ተግባራትን ጉባኤው በጥልቀት እንደሚገመግም አመልክተዋል።

"ሌብነትና ሙስናን ለመከላከል እንዲሁም የህዝብና የመንግስት ሃብት ለታለመለት ዓላማ እንዲውል የተቋቋመው የፀረ ሙስና ኮሚቴ እንቅስቃሴዎችን ውጤታማ ለማድረግ ቋሚ ኮሚቴዎች የሰሯቸው ሥራዎችም በጉባኤው ይገመገማሉ" ሲሉም አፈጉባኤዋ ገልጸዋል።

የተቋቋመው ኮሚቴም ከምክር ቤቱ ጋር ተቀናጅቶ የፀረ ሙስና ተግባራት በህዝባዊ ንቅናቄና ድጋፍ የሚፈለገውን ውጤት እንዲያመጡ የተከናወኑ ሥራዎች፣ የተዘረጉ አሰራሮች እና አደረጃጀቶችን ምክር ቤቱ እንደሚፈትሽም ወይዘሮ ፈቲህያ አመልክተዋል።

አፈጉባኤዋ አያይዘው እንደገለጹት የምክር ቤቱ የተለያዩ ቋሚ ኮሚቴዎች ቁጥጥር እና ክትትል ለማድረግ የአንድ ወር የመስክ ግምገማ አካሂደዋል።

"በእዚህም ባለፉት ስድስት ወራት በአስፈፃሚው የተከናወኑ ሥራዎች እና የህዝብን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በተሻለ ደረጃ ላይ መሆናቸውም ተመልክቷል" ብለዋል።

እንደ ወይዘሮ ፈቲህያ ገለጻ ነገና ከነገ በስቲያ ለሁለት ቀናት በሚካሄደው መደበኛ ጉባኤ ምክር ቤቱ የተለያዩ ሹመቶችን ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም