በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል- አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር

163

አዲስ አበባ (ኢዜአ ) ጥር 26/2015 በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን አጋርነት ለማጠናከር ያለመ ውይይት ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሄዷል፡፡

በዚሁ ወቅት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አገኘሁ ተሻገር እንደገለጹት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሪፎርም ከተካሄደ በኋላ አበረታች ተግባራትን ማከናወን ተችሏል፡፡

ድርጅቶቹ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት የሚደረገው ጥረት በማገዝ ፣ ልማትና የዜጎች ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ከምክር ቤቱ ጋር በመተባበር የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡

እንደዚሁም በሰላምና ዴሞክራሲ ግንባታ ላይ በመሳተፍ በኢትዮጵያ የተጀመረውን የኅብረ-ብሔራዊ ፌዴራሊዝም ግንባታ ስኬታማ የማድረግ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡

በፌዴራሊዝም ስርዓት ውስጥ የዜጎች ፍትሃዊ ተጠቃሚነትና ፍትሃዊ የመሰረተ ልማት ስርጭት ትኩረት ከሚሰጣቸው ጉዳዮች ውስጥ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ጂማ ዲልቦ በበኩላቸው የኢትዮጵያን የልማት ግብ ለማሳካት ግንባር ቀደም ከሆኑ ባለድርሻዎች መካከል የሲቪል ማህበረሰቡ ይገኝበታል ብለዋል፡፡

ዘርፉ የፖለቲካ ሆነ የንግድ ትርፍ የማግኘት ዓላማ የሌለው ከመሆኑ ባለፈ የማህበረሰቡን ችግር ለመፍታት አተኩሮ የሚሰራና ሰብዓዊነትን መሰረት ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በነበረው የተሳሳተ ፖሊሲ ምክንያት ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ማግኘት ያለባትን ጥቅም ሳታገኝ መቆየቷን አስታውሰዋል፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በቀጣይ በአጋርነት እና በትብብር ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ የሚፈራረሙ መሆኑ በውይይት መደረኩ ላይ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም