የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ፕሪሚየም 'ዋስትና' በመክፈል የኢንሹራንስ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን አስታወቀ

98

አዲስ አበባ ኢዜአ ጥር 26/2015 ከመደበኛው አገልግሎት በተጨማሪ ፕሪሚየም 'ዋስትና' በመክፈል የኢንሹራንስ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት አስታወቀ፡፡

የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሃና አርአያሥላሴ ተቋማቸው ለአገር ዕድገትና ብልጽግና አስተዋጽኦ የሚያደርጉ አዳዲስ አሰራሮችን በመተግበር ቀልጣፋ አገልግሎት ለህብረሰተቡ ለማዳረስ እየሰራ ይገኛል።

በዚህም በበጀት ዓመቱ የአገልግሎት፣ የፍጥነትና የደህንነት ችግሮችን በመቀነስ ትርፋማነቱን ማሳደግ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

ተቋሙ ከዚህ በፊት ከሚሰጣቸው አገልግሎች በተጨማሪ አዳዲስ አገልግሎቶችን ለደንበኞች ለማድረስ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከነዚህ መካከል ደንበኞች ከፍተኛ ዋጋ ያላቸውን እቃዎች ማንቀሳቀስ ሲፈልጉ ከመደበኛው አገልግሎት በተጨማሪ ፕሪሚየም በመክፈል የኢንሹራንስ አገልግሎት መስጠት መጀመሩንም አብራርተዋል፡፡

ፕሪሚየም ተጠቃሚዎች ትላልቅ እቃዎችን ማንቀሳቀስ ሲፈልጉ ከአዳጋ ነጻና በንብረቱ ላይ የሚደርሰውን ስጋት በመቀነሰ በልበ ሙሉነት እንዲገለገሉ የሚረዳ ነው።

በበጀት ዓመቱ የትራንዚት ኢ-ኮሜርስ አገልግሎትን ወደ ተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ተደራሽ እያደረገ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡

ባለፉት 2 ወራት ብቻ ወደ ስድስት የአፍሪካ አገራት ከ80ሺ በላይ እቃዎችን ለመላክ ሂደት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ሰዎች ወደ ፖስታ ቤት ቅርንጫፍ መምጣት ሳይኖርባቸው ባሉበት ቦታ መገልገል እንዲችሉ የኢኤምኤስ ወይም ኤክስፕረስ ሰርቪሶችን በመስጠት በኩል በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል ነው ያሉት፡፡

በዚህም ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ በኢኤምኤስ /በዘመናዊ መልዕክት መለዋወጫ/ ከተቀበላቸው መልዕክቶች መካከል 70 ከመቶውን ለደንበኞቹ ባሉበት ቦታ የማድረስ ስራ ማከናወኑን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት በአገር አቀፍ ደረጃ ከ700 በላይ ቅርንጫፎች አሉት።

ድርጅቱ ላለፉት 129 ዓመታት ዓለም አቀፍ የፖስታ አገልግሎት በመስጠት ታሪክ ያለው አንጋፋ ተቋም መሆኑ ይታወቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም